ለመስማት መቅረብ…
እግዚአብሔር ተናጋሪ አምላክ ነው፡፡ ሐሳብ ስላለው ይናገራል፤ ዓላማ ስላለው ይናገራል፤ ግብ ተኮር ስለሆነ ይናገራል፤ አፍቃሪም ስለሆነ ይናገራል፡፡ ከመጀመሪያው አንስቶ ሲናገር ነበር፡፡ ፍጥረትን እንኳ ወደ መኖር ያመጣው አናግሮ ነው፡- “ይሁን” እያለ፡፡ ሲፈጥር እንደ ተናገረ፤ ከፈጠረም በኋላ ተናግሯል፤ ባርኳል፡- “ብዙ ተባዙ…ግዟቸው” (ዘፍ 1፥28) ብሎ፤ መመሪያ ሰጥቷል፡- “አትብላ…ትሞታለህ” ብሎ (ዘፍ 2፥17)፡፡ ሰው ሲወድቅም መናገር ቀጠለ፣ “የት ነህ?” (ዘፍ 3፥9) ብሎ፡፡
የዕብራውያን ጸሐፊ መልእክቱን ሲጀምር ለየት አድርጎ ነው፡፡ ለዚህም ነው አንዳንዶች መጽሐፉ እንደ ‘አካዳሚያዊ’ ጽሑፍ (ኤሴይ) ጀምሮ፣ እንደ ስብከት ይቀጥልና እንደ ደብዳቤ ይጠናቀቃል የሚሉት፡፡ ይሄው መልእክት እንዲህ ብሎ ይጀምራል፡- “እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በተለያየ ጊዜና በልዩ ልዩ መንገድ በነቢያት በኩል ለአባቶቻችን ተናግሮ፣ በዚህ መጨረሻ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገውና ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ ለእኛ ተናገረን” (ቁ.1-2)፡፡
ሰዉና መንገዱ (በእሳት፣ በድምፅ፣ በህልም፣ በዝምታ ድምፅ…) ይለያይ እንጂ እርሱ ሲናገር ኖሯል፡፡ የንግግሩ ማጠቃለያ ደግሞ በጌታ በኩል ተሰጥቷል፡፡ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ በትስጉት (ቃል ሥጋ በመሆኑ)፣ በሕይወቱ፣ በአደራረጉና በትምህርቱ የእግዚአብሔር መልእክት ነበር፡፡ በእርሱ በኩል ያላለፈ ነገር የለም፡፡ ከእርሱ ጋር የነበሩና ከእርሱ የሰሙም ለእኛ ሁሉን አስቀሩልን፡፡
እንግዲህ የእግዚአብሔር ፊተኛም ሆነ ኋለኛ ንግግር በእጃችን ነው ያለው፤ በመጽሐፍ ቅዱስ መልክ፡፡ ይህንን ቃል ብንታይበት እንነጻለን፤ ብናምነው እንቀየርበታለን፤ ብናከብረው፣ እንከበራለን፤ ብንጠጋው፣ ኀይል ይሆንልናል፡፡
የመረጃ ክምችት በበዛበትና ብዙ አማራጭ፣ ውክቢያና ውድድር ባለበት በዚህ ዘመን ለመጽሐፉ ተገቢውን ማዕረግ (ክብር) መስጠት የሚቸግራቸው ብዙዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እንደ እነዚህ ዐይነት ሰዎችም ለጊዜው ግብዣ ዘመናዊ ምላሽ መስጠት አስፈላጊ አንደ ሆነ በማመን የመጽሐፉን ደረጃ ያወርዳሉ ወይም ሌሎችን መረጃዎች (ጽሑፎች ወይም ሰዎች) ያለ ቦታቸው ከፍ አድርገው ያስቀምጣሉ፡፡
“አናንተ ግን” ይህንን ታደርጉ ዘንድ አይገባም፡፡ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን እንዲህ ብሎ አሳሰበው፤ “አንተ ግን በተማርኸውና በተረዳኸው ጽና፤ ይህን ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤ ከሕፃንነትህም ጀምረህ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳት መጻሕፍትን ዐውቀሃልና” (2ጢሞ 3፥14-15)፡፡ ይህ ዕውቀትና ጥበብ ከሌላ ስፍራ የሚቀዳ አይደለም፡፡ እነዚሁ መጻሕፍት “የእግዚአብሔር መንፈስ” ያለባቸው ስለሆኑ ጊዜን የሚያልፉ፣ ሥልጣኔን የሚቀድሙና ዘመንን ሁሉ የሚያስረጁ ናቸው፡፡
ተመራቂዎች ሆይ!
የተማራችሁትን ሁሉ ወደ ኋላ የማትመለከቱበት ጊዜ ላይ ደርሳችኋል፡፡ አውቃችሁ አለፋችሁ፤ አልፋችሁም ተመረቃችሁ! ከእንግዲህ ያው ንባብ ለሥራ እንጂ ለማለፍ አይገለጥም፡፡ በእጃችሁ ያለው የእግዚአብሔር ቃል ግን የዘወትር ምግብ፣ የሁልጊዜም መመሪያ ነው፡፡ ቃሉን ያጻፈው መንፈስ ጊዜን የቀደመ፣ ወደ ፊት ያለውንም ጨርሶ (አንድም ሳይቀር) ያወቀ ነው፡፡ ዮሐንስ ባይኖር እርሱን ያነሳሳና ያጻፈ መንፈስ ሁሌም ሕያው ነው፤ ጳውሎስ ቢሰዋም፣ በእርሱ የሠራና ያለፈው የዕውቀትና የጥበብ፣ የኀይልና የቅድስና መንፈስ ከቃሉ ጋር አብሮ ዘልቋል፡፡
ዛሬ ደማቅ፣ ነገ ደግሞ ብሩኀ እንዲሆንላችሁ ይህንን ቃል አንብቡት፣ አጥኑት፣ አውሩት፣ ተጫወቱትም፡፡ እግዚአብሔር ሁሉን በልጁ ቢናገርም፣ ሁሉንም አልሰማንም፤ የሰማነውንም ቢሆን በደንብ አላሰላሰልነውም፡፡ ብዙ ዘመን፣ በርካታ አጋጣሚም ከፊታችሁ አለ፡፡ ሁሉን በደንብ የምታልፉበትና የምታስተናግዱበት ቃል ደግሞ በእጃችሁ ተሰጥቷችኋል፡፡ ኑሩበት፤ እግዚአብሔርም በነገር ሁሉ ከእናንተ ጋር ይሆናል፡፡
ናሁሠናይ አፈወርቅ
የቢብሊካ ኢትዮጵያ ዋና ፀሐፊ