በኮቪድ19 ምክንያት የተቋረጡትን በኢቫሱ ሕብረቶች ሲደረጉ የነበሩትን የንዑስ ቡድኖች እንዴት ማስቀጠል ይቻላል?
“ስማርት” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል፤ ጉብዝናን፣ ፍጥነትንና ቅልጥፍናን አመልካች ሲሆን በ21ኛው ክፍለዘመን በተጨማሪነት ኢንተርኔትን ለሚጠቀሙ ቁሶችም በገላጭነት እንጠቀምበታለን፡፡ በሚከተለው አጭር ጽሑፍ በየካምፓሶቹ በኢቫሱ ሕብረቶች ሲደረጉ የነበሩትን የንዑስ ቡድኖችን በኮቪድ19 ስለተቋረጡ ዘመኑ ባጎናፀፈን የመገናኛ ቴክኖሎጂ ተጠቅመን እንዴት ማስቀጠል እንደሚቻል እንመክራለን፡፡
የኢቫሱ ዋና ዓላማ “ተማሪዎችን በማገልገል የእግዚአብሔርን መንግስት ማስፋት” ነዉ፡፡ ከዚህም የተነሳ ተማሪዎች በግቢ ቆይታቸዉ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ጌታቸዉ እና አዳኛቸዉ እንዲከተሉ እንዲሁም ከዚህ ምልልስ የወጣ የምስክርነት ሕይወት (የቃል እና የኑሮ) እንዲኖራቸዉ በትጋት ይሰራል፡፡ ይህንንም ዓላማ ከግብ ለማድረስ እንደ ዋና የአገልግሎት ስልት የሚጠቀመው የንዑስ ቡድን አገልግሎትን ነው፡፡
የንዑስ ቡድን አገልግሎት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት ያለዉና ለመንፈሳዊ እድገት እና ለአገልግሎት፡- ተሳታፊነትን፣ ተደራሽነትን እና ተጠያቂነትን የሚያመቻች ቦታ ነዉ፡፡ የንዑስ ቡድንን ጠቀሜታ በተለያየ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መመልክት እንችላለን፡፡በብሉይ ኪዳን የሙሴ አማት የሆነዉ ዮቶር፣ ቀኑን መሉ ህዝቡን እየዳኘ ለነበረዉ ሙሴ ሕዝቡን በንዑስ ቡድን (10፣50፣100፣10000) አድርጎ በማዋቀር የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሰጥና ከራሱ ላይ ጫናን እንዲቀንስ የጥበብ ምክርን ሲያካፍላዉ እንመለከታለን፡፡(ዘፀ 18፡17̄-23) አካን የተባለ ሰዉ ከሰናዖር ምርኮ የመጡ ዕርም በሆኑ ዕቃዎች በመጎምጀቱ ምክንያት ወስዶ እንደደበቃቸዉ ፤ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር ቁጣ እንደነደደ ከዚህ በፊት ከነበሯቸው ጦርነቶች ጋር ሲወዳደር ቀላል በሚባለዉ ከጋይ ጋር ባደረጉት ጦርነትም እንደተሸነፉ ይናገራል፡፡ ይህንንም ሰው(አካንን) ከመላው እስራኤል መኃል የለዩበት መንገድ የእስራኤልን ቤተሰብን ማዕከል ያደረገ የንዑስ ቡድን አወቃቀር እንደነበር ግልጽ አድርጎ ያሳያል፡፡ (ኢያ.7፡14 -15)
በብሉይ ኪዳን እግዚያብሔር፤ ቤተሰብን መሰረት ያደረገ ንዑስ ቡድን የተለያዩ አላማዎቹን ለማስፈፀም ተጠቅሟል፡፡ ከዚህ ዉስጥ አንዱ እያንዳንዱ ቤተሰብ ለልጆቹ ስለ እግዚያብሔር ማንነት፣ ለእስራኤልም ስላደረገዉ ነገር፤ ህጉንና ስርዓቱንም እንዲያስተምሩበት ያደረገዉ ነዉ፡፡ ይህም እስራኤል በየትዉልዱ የእግዚያብሔር የቃልኪዳን ህዝብ ሆና እንደትቀጥል ዓላማ ያደረገ ነበር፡፡
በአዲስ ኪዳንም ይህንን የንዑስ ቡድን አሰራር በተመሳሳይ መንገድ እንመለከታለን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረዉ ቆይታ ዉስጥ ዓላማዉን፣ መንገዱንና ሕይወቱን በጥልቀት ለማካፈል የመረጠዉ 12 ሰዎችን የያዘ ንዑስ ቡድን ነበር፡፡ ከዚያም ቀጥሎ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 ላይ ከኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት በኋላ መንፈስ ቅዱስ እንደወረደ እንመለከታለን።ከዚህም ጋር ተያይዞ ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ባደረገዉ ስብከት 3000 ሰዎች በቁጥራቸዉ ላይ ተጨመረ፡፡ እነዚህም አማኞች (ቁ. 46) ላይ ‘በየዕለቱ በቤተ መቅደስ በአንድነት እየተገናኙ፣ በቤታቸዉም እንጀራ እየቆረሱ በደስታና በቀና ልብ ይመገቡ’ እንደነበር ይናገራል፡፡ ይህ ክፍል እንደሚናገረዉ በአንድ ጊዜ ቁጥሩ እጅግ የበዛዉ ይህ ጉባዔ አንድም በአንድነት ቤተመቅደስ የመገናኘት ጊዜ ነበረዉ (ይህ ሁሉንም በአንድነት የሚያገናኝ መድረክ ነው) በየቤታቸዉ እንጀራን የመቁረስ (ሕብረትን የማድረግ) ጊዜ ነበረዉ (ይህ በትንንሽ ቁጥር ሆነው እምነታቸውን የሚለማመዱበት መድረክ ነው)::
ሌሎቹም የአዲስ ኪዳን ክፍሎች የሚያስተምሩን መጽሐፍ ቅዱሳችን የጥቂት ሰዎች አገልጋይነት የሌሎች ደግሞ ተገልጋይነትን/ተመልካችነተትን/ታዳሚነት የሚያበረታታ መጽሐፍ ሳይሆን የእያንዳንዱን አማኝ አገልጋይነት የሚያስተምር መጽሐፍ እንደሆነ ነዉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳችን እያንዳንዱ አማኝ የጸጋ ስጦታን እንደተቀበለ፣ እንደ አካል ብልት የአንዱ የጸጋ ስጦታ ለሌላዉ እንደሚያስፈልግ ያስተምረናል፡፡ (1ኛ ቆሮ ምዕራፍ 12) ይህንንም በጥልቀት መለማመድ የሚቻዉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ካሉበት ጉባዔ ይልቅ በትንንሽ ቁጥር በተደለደሉ ንዑስ ቡድኖች ነዉ፡፡ ቀድሞ እንደተጠቀሰው ንዑስ ቡድን ለመንፈሳዊ ሕይወት እድገትና ለአገልግሎት፡- ተሳታፊነትን፣ ተደራሽነትን እና ተጠያቂነትን (Accountablity)ን በመፍጠር የሚያገለገል አይነተኛ አሰራር ነዉ፡፡
እንግዲህ እኛም በሐዋ. 2፡42-47 ያለዉን ፈለግ በመከተል እየሰራን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ተማሪዎች በየሕብረቶቻቸው (Campus Fellowships) በአንድነት እግዚአብሄርን የሚያመልኩበት ጊዜ እንዲኖራቸዉ እንዲሁም በንዑስ ቡድን ሆነዉ እምነታቸዉን የሚለማመዱበት፣ ይኸዉም በሐዋ2፡42-47 መሰረት – የእግዚአብሄርን ቃል የሚያጠኑበት፣ የሚጸልዩበት፣ ህብረትን የሚያደርጉበት እና ወንጌልን ለመመስከር የሚበረታቱበት ጊዜ እንዲኖራቸዉ ይጠበቃል::
ይህንንም የንዑስ ቡድን አገልግሎት በሚገባ ለማደራጀትና ለማካሔድ በየሕብረቱ በዋናነት የሕብረት መሪ የሆኑ ተማሪዎችና የንዑስ ቡድን መሪዎች በትጋት እየሰሩ ይገኛል፡፡ እንግዲህ በድንገት የተከሰተዉ ይህ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት በእንደነዚህ አይነት የንዑስ ቡድኖች ዉስጥ እየተሳተፋችሁ የመንፈስ ቅዱስንም ጸጋና በረከት እየተካፈላችሁ እንደነበረ እናምናለን፡፡
አሁን ተማሪዎች በየቤታችሁ ባላችሁበት ወቅት ታዲያ ከዚህ በረከት መካፈልን እንዴት እንቀጥል ብሎ ማሰብ አስፈላጊ ነዉ፡፡ የንዑስ ቡድን ሕብረታችንን በዚህ ጊዜ መቀጠሉ ለምን ይጠቅመናል?
1. አጋጣሚ በሚመስል ሁኔታ የተሰጠንን ይህንን ጊዜ በአግባቡ ለመጠቀም ይጠቅመናል፤
2. በእጃችን ላይ ያለዉን የኢንተርኔት አገልግሎት በአግባቡ ተጠቅመን እንድናተርፍበት ይረዳናል፤
3. ብረት ብረትን፤ ባልንጀራም ባልንጀራውን ይስለዋል እንደሚል ከጓደኞቻችን፣ ከእድሜ እኩዮቻችን ጋር በእግዚያብሔር ቃል ዙሪያ በመቀመጥ እንድንሳሳል ያደርገናል፤
4. በካምፓስ ዉስጥ ከእግዚያብሔር ለተሰጠን የወንጌል አደራ በጋራ እንድንተጋ ያያይዘናል፤
5. ወደ ግቢ (Campus) ስንመለስም ካቆምንበት ለመቀጥል ይቀለናል።
ታዲያ በየንዑስ ቡድናችን ያለዉን ሕብረት እንዴት መቀጠል እንችላለን?
በዚህ ዙሪያ እያንዳንዳችን በተለይም የንዑስ ቡድን መሪዎች በስራችን ያሉ ተማሪዎችን ሁኔታ እና ያሉንን እድሎች በማጤን ለንዑስ ቡድናችን የሚስማማዉን መንገድ መፈለግ ይኖርብናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በስፋት እንደሚስተዋለው የኢንተርኔት አገልግሎትን መጠቀም በምንችል ንዑስ ቡድኖች ዉስጥ የቴሌግራም ግሩፕ በመክፈት መጠቀም እንችላለን፡፡ ይህንን አገልግሎት ለመጠቀም ውሱንነት ካለ ደግሞ የስልክ አገልግሎት፣ የአጭር የጽሁፍ አገልግሎትን መጠቀም እንችላለን፡፡
ቀጣዪ ጥያቄ “በእነዚህ የመገናኛ ዘዴዎች ተጠቅመን ምን እናድርግ?” የሚል ነዉ
ከላይ እንደተጠቀሰዉ ንዑስ ቡድናችን ሐዋ. 2፡42-47ን መሰረት በማድረግ 4 ይዘቶች አሉት እነዚህም የእግዚያብሔር ቃል ጥናት፣ ጸሎት አና አምልኮ፣ ሕብረትና የወንጌል ተልእኮ ናቸዉ፡፡በቀጣይ በእያንዳንዱ ይዘቶች ስር ልናደርጋቸዉ የምንችላቸዉ እና እንደመነሻ ሃሳብ የሚያገለግሉ ሃሳቦችን እጠቁማለሁ፡፡
የእግዚያብሔር ቃል
ሀ) በየሳምንቱ/ በየለቱ እንደየዉሳኔያችን አንብበን በማሰላሰል የተረዳነዉን ነገር የምንከፋፈልበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በመስጠት
ለ) የመጽሀፍ ቅዱስ ንባብን ለማበረታታት የተወሰነ የመጽሃፍ ቅዱስ ክፍልን/ ለምሳሌ አዲስ ኪዳንን/ ለማንበብ በመወሰን አንዳችን ለሌላችን ተጠያቂ መሆን
ሐ) ድምጽን ቀድቶ በመላክ የእግዚያብሔር ቃል መከፋፈል
መ) ለመንፈሳዊ እድገት የሚረዱ መጽሃፎችን ለማንበብ መበረታታትና ያሉንን የመጽሀፍ ፋይሎች መላላክ ጥቂቶቹ ናቸዉ፡፡
ጸሎትና አምልኮ
ሀ) ስለ ወረርሽኙ ጨምሮ የጸሎት ርእሶችን መለዋወጥ
ለ) በቀን ዉስጥ ሁላችንም በጸሎት የምንሆንበትን ጊዜ መመደብ
ሐ) እንደ chain prayer አይነት መንገዶችን መጠቀም
መ) ዝማሬዎችን እና ለጸሎት የሚያነሳሱ ጽሁፎችን መላላክ
ሕብረት
ሀ) አሁን በአካል ባንገናኝም በስልክ እየተደዋወሉ መጠያየቅ እና በመካከላችን ያለዉን ግንኙነት ማሳደግ፤
ለ) በንዑስ ቡድናችን አባል የሆኑ ተማሪዎች ቢጎዱ ቢታመሙ ወይም ቢቸገሩ በምንችለው ሁሉ መርዳት፤
ሐ) ለትምህርታችን ጠቃሚ የሆኑ ማቴሪያሎችን በመላላክ መደጋገፍ እንችላለን፡፡
የወንጌል ተልእኮ
በካምፓስ ዉስጥ እያለን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠንን የወንጌል አደራ (ማቴ.28፡18-20) ለካምፓስ ተማሪዎች ማድረስ በዋናነት በእኛ ላይ ይወድቃል፡፡ በመሆኑም በዚህ ግዜ እንኳን ይህንን የምስራች ልንነግራቸዉ ላሰብናቸዉ ሰዎች በመጸለይ እየደወሉ ሆንብሎ ወዳጃዊ ግንኙነትን በመፍጠርና ምቹ ሁኔታ ሲገኝ ወንጌልን በመናገር ልንተጋ ይገባል፡፡ ለዚህም ስራ በንዑስ ቡድናችን በኩል ልንተዋወስ፣ ልንጠያየቅ እና ልንበረታታ እንችላለን፡፡
በመጨረሻም ንዑስ ቡድን ኖሮን እንኳን በሚገባ ለመስራት እድል ያላገኘን የንዑስ ቡድን መሪዎች፣ ተማሪዎች በዚህ ግዜ ነፃ የሚሆኑበት እና ህብረትን፣ መጠየቅን የሚፈልጉበት ጊዜ ስለሆነ፤ ቡድናችንን ለመመስረት እና ለማስተዋወቅ ወደ ጊቢ ስንመለስም አጠናክሮ ለመያዝ እድል ስለሚሰጠን ይህንን እድል እንድንጠቀምበት እመክራለሁ፡፡
ጌታ ይባርካችሁ፡፡
Author: Rekik Hailu, Students Ministry Officer in EvaSUE