የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ተማሪዎችና ምሩቃን ማሕበር(ኢቫሱ)፣ ከተመሰረተ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ ከምስረታው (ከ1957 ዓ.ም) ጀምሮ ወንጌላውያን ክርስቲያን ተማሪዎችን ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ ማኅበሩ ፣ አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ፣ የእግዚአብሔር መንግስት በዩኒቨርሲቲና ኮሌጆች ውስጥ እንዲሰፋ እየሰራ ይገኛል፡፡ በእስከአሁኑ አገልግሎቱም፣ ቁጥራቸው ብዙ የሆኑ የቤተክርስቲያን እና ሀገር መሪዎችን፣ አገልጋዮችን፣ በክርስቲያናዊ ሥነ-ምግባር የታነፁ ባለሙያዎችን ማፍራት ችሏል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ፣ በከፍተኛ ተቋማት የሚገኙት ወንጌላውያን ክርስቲያን ተማሪዎችን ሕብረቶች እያገለገለ የሚገኘው፣ ይኸው ተቋም(ኢቫሱ)፣ ከተመሰረተ ሃምሳ ሦስት(53) ዓመት ሆኖታል፡፡
በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች ታሪክ፣ የተማሪዎች አገልግሎት ሚና
ኢቫሱ፣ የካቲት 15/2010.ዓ.ም፣ ለቤተክርስቲያን መሪዎችና አጋር አካላት ባዘጋጀው የአንድ (1) ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ የውይይት መድረክ ላይ ፣ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ተማሪዎችና ምሩቃን ማኅበር (ኢቫሱ)፣ በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች ታሪክ የተማሪዎች አገልግሎት ሚና በሚል ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ ጽሑፉ የቀረበው በወንድም ጌቱ ግዛው ነበር።
ወንድም ጌቱ፣ በጽሑፋቸው እንዳመለከቱት ኢቫሱ፣ ሕብረት (fellowship)፣ እንቅስቃሴ(Movement)፣ እንዲሁም ተቋም( Organization) መሆኑን አመልክተው፣ ከታሪኩ እንደምንረዳው ከድርጅት ቅርጽ ይልቅ እንቅስቃሴ መሆኑ ጎልቶ ይታይ እንደነበር አመልክተዋል፡፡ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጥንስሱ የተጀመረው በወቅቱ በነበሩ እንደ ሐሮማያ እርሻ ኮሌጅ፣ ጅማ ጤና ሣይንስ ኮሌጅ፣ ሐረር መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅና እነዚህን በመሳሰሉት ሌሎች ኮሌጆች እንደነበር በጽሑፋቸው አስረድተዋል፡፡ ኢቫሱ፣ እንደ ህብረት መልክ ይዞ ለመመስረት የበቃው ፣ በ 1957 ዓ.ም በጥቂት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ክርስቲያን ተማሪዎች ስብስብ እንደነበር ጽሑፉ ያትታል፡፡
በጽሑፉ ከተጠቀሱት ሌሎች አበይት ጉዳዮች መካከል፣ የተማሪዎች አገልግሎት አስተዋጽኦ በኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች ዘንድ የሚለው ይገኝበታል፡፡
ከነዚህም መካከል፡-
♣ በንዑስ ቡድን የሚካሄድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይገኝበታል፡፡ የጥናት ስልቱ ከዝርዝር ወደ ድምዳሜ የሚደርስ (Inductive Bible Study) ሆኖ ማስተዋል (Observation) ፣ መተርጎም (Interpretation) ፣ ከራስ ጋር ማዛመድ (Application) የሚሉ ክፍሎች አሉት:: ይህን የአጠናን ስልት ለቤተክርስቲያን በማስተዋወቅ ረገድ፣ ኢቫሱ እንደ አንደ አገልግሎትና ምሩቃን የሆኑ ወጣቶች ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ዶ/ር መልሳቸው መስፍን እና ዶ/ር አለም ባዘዘው ወደ ገነት ቤ/ክ ይዘውት መጡ ሲሉም ተናግረዋል፡፡
♣ ኢቫሱ፣ ቤተእምነቶችን በጋራ በማስተባበር በአንድነት እንዲሰሩ ያደረገ፣ ለኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ልዩ ውበት የሆነ አንድነት ለመፍጠር የተጫወተው ሚና ቀላል አይደለም፡፡
♣ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ውስጥ፣ የእግዚአብሔርን ቃል የሚወዱ፣ የተቃኙ ፣ የበሰሉ የአብያተክርስቲያን ልዩ ልዩ መዋቅርና የቤተክርስቲያን አጋዥ አገልግሎት መሪዎችን ለማፍራት ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡
♣ በየዘመናት በኮሚንዝም፣ በሐሰተኛ ትምህርትና በዘረኝነት ዝንባሌዎች ላይ የነብይነት አገልግሎት ሰጥቷል፡፡
♣ አብያተክርስቲያናት በወንጌል ስራ እንዲጠመዱና ይህን ተልዕኮ ችላ እንዳይሉት የተማሪዎች አገልግሎት ትልቅ ሚና ነበረው፡፡
በጽሑፉ ውስጥ በየዘመናቱ ስለ ኢቫሱ የተነሱ አሉታዊ አመለካከቶችም ተጠቅሰዋል፡-
- ኢቫሱ ቤተክርስቲያን እየሆነ ነው፣
- ኢቫሱ አይመጋገብም ፎካከራል እንጂ፡፡ አገልጋዮችን፣ ምእመናንን በጊዜያቸው፣ በገንዘባቸው እና በእውቀታቸው የቤተክርስቲያን ተሻሚ ሆኗል፣
- ብዝኃ ቤተእምነት አቋም ቢኖረውም ወጣቶችን ወደተወሰኑ ቤተእምነቶች ያፈልሳል፣
- ተማሪዎች ጨርሰው ለእረፍት ሲመለሱ በቀላሉ ወደ አጥቢያ ቤተክርስቲያናቸው እንዳይመሰሉ አድርጓል፣
- ከምርቃት በኋላ ወደ ቤተክርስቲያናቸው እንዳይመለሱ በሌላ ህብረት ስም ይይዛቸዋል፣
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት አሉታዊ አስተሳሰቦች የግንዛቤ ችግር የፈጠራቸው እንጂ አንዳቸውም እውነትነት እንደሌላቸው በልዩ ልዩ አካላት መልስ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ኢቫሱ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በሚዘልቀው ታሪኩ ሲያደርግ እንደነበረው፣ የቤተክርስቲያን አጋዥና አጋር አገልግሎት ሆኖ እንደሚቀጥል ተጠቅሷል፡፡
በመጨረሻም፣ በጽሑፉ ማጠቃለይ እንደተገለጸው፣ ይህ የተማሪዎች አገልግሎት ሊሻሻሉ የሚገባቸው ድክመቶች ቢኖሩበትም በአብያተክርስቲያን ዘንድ በቂ ድጋፍ እየተደረገለት አይደለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ይህ ካልተቀየረ ተጎጂዋ ቤተክርስቲያን እንደምትሆን በማሳሰብ፣ አገልግሎቱን በምንችለው ሁሉ እንርዳ የሚል የማጠቃላያ ሐሳብ ጽሑፋቸውን አጠናቀዋል፡፡
ወንድም ጌቱ ግዛው፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፋርማሲ ትምህርት ቤት ተማሪ በነበሩበት ጊዜ በተማሪዎች ሕብረት ውስጥ ንቁ ተሣታፊ ነበሩ፣ እንዲሁም ከምርቃት በኋላ ፣ በኢትዮጵያ ገነት ቤተክርስቲያን በፕሬዝዳንትነት፣ በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት ሕብረት ውስጥ በምክትል የቦርድ ሰብሳቢነት፣ በኢቫሱ የቦርድ አባልነት እንዲሁም በሌሎች ቁጥራቸው የበዛ ተቋማት ውስጥ ሲያገለግሉ የቆዩና በማገልገል ላይ ያሉ ወንድም ናቸው፡፡