ገበያን ሳስበው ገና ከቤቴ ሳልወጣ ድካም ይሰማኛል፣ ግን ደግሞ የግድ መርካቶ መሄድ ነበረብኝ፣ ጫማ ልገዛ፤ ደግሞ እግሬ ትልቅ ነው (አርባ ቁጥር)፣ ጫማ ሻጮች ሁሌም ግርም ይላቸዋል፡- የቁመቴ ማነስና የእግሬ መተለቅ፣ እኛ አገር ደግሞ ትልቅ ቁጥር ጫማ እንደ ልብ አይገኝም፤ እህቴ “ጫማው ነው የሚመርጥሽ” እያለች ትቀልድብኝ ነበር፡፡ ወሩ ጥቅምት እንደነበር ትዝ ይለኛል ዓመተ ምህረቱ ደግሞ 2002፤ እንዴትስ እረሳዋለሁ?! የመዞር ስንፍናዬን በደንብ የሚያውቀው ባለቤቴ አስጠንቅቆኝ ነበር “በይ ደግሞ ተወደደ፣ የሚሆነኝ ጫማ አጣሁ ብለሽ የማይረባ ጫማ ገዝተሽ እንዳትመጪ” ብሎ፡፡ ትንሽ ዞር ዞር እንዳልኩኝ ጥራት ያለው ጫማ ዋጋ በእጥፍ መጨመሩን አየሁ፤ ስለሆነም አንዱን ጫማ በምገዛበት ገንዘብ ሁለት የመግዛት ዕድል እንዳለኝ አሰብኩኝ፣ “ግን ደግሞ መንገደኛ ነኝ ብዙ ብር ባላወጣስ?” አልኩኝ ለራሴ፣ አንድ ጫማ ይበቃኛል ብዬ ወሰንኩኝና ደህና የመሰለኝን ጫማ እጅግ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ገዝቼ ተመለስኩኝ፣ ባለቤቴ እስኪያየው ቸኩያለሁ፡፡
በማግስቱ የውጭ ጉዞ ነበረብኝ እና አዲሱን ጫማዬን ሳደርግ “ተይ” አለኝ ባለቤቴ “አዲስ ጫማ ተደርጎ አይኬድም፣ ባይመችሽስ?” ልሰማው ፈቃደኛ አልነበርሁምና ቦሌ አድርሶኝ ከእጅ ቦርሳዬ በቀር ዕቃዬ በሙሉ መግባቱን አረጋግጦ ተመለሰ፡፡ ውስጥ ገብቼ ቆየሁኝና ቁጭ ማለቱ ስለደከመኝ ሱቆቹ አካባቢ በአዲሱ ጫማዬ ጎርደድ ጎርደድ ስል ድንገት የቀኝ እግሬ ክፉኛ ቀለለኝ፣ ክው ብዬ ዞር ስል የአዲሱ ጫማዬ ሶል ተገንጥሎ የላይኛው ክፍል እግሬ ላይ ቀርቷል፣ አይ ፈጣን ነገር የመውደድ ጦስ! አይ ጊዜ ያለመስጠት መዘዝ! አይ ሰውን አለመስማት!
አቋራጭ መንገድ፣ ፈጣን ሥራ፣ ፈጣን ዕድገት፣ ፈጣን ለውጥ፣ ፈጣን ምግብ፣ ወዘተ መፈለግ የአብዛኛው ሰው ፈተና ነው፤ መጠበቅ፣ መታገስ፣ ጊዜ መስጠት፣ ከመዝገበ ቃላታችን የተሰረዙ ይመስል ሁሉም ሰው ይፈጥናል፤ የኮርስ ማሟያ የቤት ሥራ ተኮርጆ፣ ፈተና ተገልብጦ፣ የመጨረሻው የመመረቂያ ወረቀት በክፍያ ተሰርቶ፣ ካልሆነም ድግሪ፣ ዲፕሎማ ተገዝቶ፣. . . በፍጥነት ወደ ሥራ፣ ሥራም እንደ ነገሩ በጥድፊያ ተሰርቶ ወዲያው ዕድገት የሚገኝበት መንገድ፣ ከመስሪያ ቤት መስሪያ ቤት መዝለል፣ ጥድፊያ፣ ችኮላ፣ ሩጫ፣ . . .
ይህ የሕይወት ዘዬ መንፈሳዊ ሕይወታችን ላይ የሚገለጠው በአቋራጭ ለማደግ፣ ለመባረክ፣ ለመጠርመስ ስንሮጥ ነው፡፡ ቃሉ ግን እንዲህ ይለናል፡- “እግዚአብሔርን ለመመስል ራስህን አስለምድ” (1ጢሞ 4፡7) ጢሞቴዎስ ጥሩ ሕይወት የነበረው ወጣት እንደሆነ ሐዋሪያው ጳውሎስ መስክሮለታል ግን ራስህን አስለምድ ይለዋል፡፡ ምን ማለቱ ነው፤
1) “ኃላፊነቱ ያንተ ነው“ እያለው ነው፡፡ ጌታን እንደ ብቸኛ ኃላፊነት እንዳለበት አድርጎ ማሰብ ትክክል አይደለም፣ ማስለመድ ያንተ ፋንታ ነው “ጌታ ሆይ አስለምደኝ” ብሎ መጸለይ ትርጉም የለውም ማለት ነው፣ ያንተን ሥራ ጌታ አይሰራልህምና፡፡ ሥጋን ከሚገዙ ነፍስን ከሚያቀጭጩ ነገሮች መራቅ ያንተ ድርሻ ነው፡፡
2) “ምንድነው የምታስለምደው?” ለሚለው እግዚአብሔርን መምሰል ነው ምላሹ፣ ይህ የባህርይ ለውጥ ላይ ማተኮርን ይጠይቃል፣ በአስተሳሰብና በግብር፤ አእምሮህን የምትመግበው ምንድነው? አዘውትረህ የምትለማመደውስ ነገር ምንድነው? ያዘወተርሽው ያለጥርጥር ይገዛሻል፡፡ ጌታ በምትሃታዊ ኃይል አያሳድግሽም፤ የዘራሽውን ታጭጃለሽ፡፡ ሰውነት እንዳስለመድከው ነው፣ ያስለመድከውን ነገር ዘወትር አምጣ ይልሃል፡፡
3) ጌታን መምሰል ራስን መግዛትን (ዲሲፕሊን) ይጠይቃል፤ ኃይሌ ገ/ሥላሴ ከብዙ ልምምድ በኋላ ነው ሻምፒዮን የሆነው፤ ሳይለማመዱ ሰውነትን ሳያለማምዱ በአንዴ ልቆ መገኘት አይቻልም፣ ልምምድ ደግሞ ጊዜን፣ ጉልበትን፣ ሙሉ ትኩረትን ይፈልጋል፡፡ አልፎ አልፎ ቃሉን በማንበብና በመጸለይ፣ አልፎ አልፎ ኅብረት በማድረግ የትም አይደረስም፡፡ የክርስትና ጉዞ አቋራጭ መንገድ የለውም፡፡
ቃሉን ማጥናት፣ መጸለይ፣ መጾም፣ ኅብረት ማድረግ፣ ማገልገል፣ መስጠት፣ ማዳመጥ፣ . . . መከራን መታገስ ግድ ነው፡፡ ፈተና ሳይታለፍ ምረቃ አለ እንዴ? ያለመከራም ዕድገትና ሥር መስደድ የለም፡፡ ልጅ ያለ ዘጠኝ ወር እንደማይወለድ ሁሉ የተፈጥሮ ዕድገቱን ሳይጠብቅ በዓመቱ ኬጂ፣ በሚቀጥለው ዓመት ሃይ ስኩል አይገባም፡፡ አንድ ሰባኪ “የዘመኑ ሰው ከዩኒቨርሲቲ የተመረቀ ልጅ ቢወልድ ደስ ይለዋል” ያለው አይረሳኝም፡፡ የተፈጥሮ ዕድገትን ማቻኮል እንደማይቻል (በእንስሳት ላይ ሲደረግ ተመጋቢውን ለበሽታ እንደሚዳርግ) ሁሉ መንፈሳዊውንም ማፋጠን አይቻልም፤ ደርሶ የሚያሳድገን ምትኃታዊ ኃይል ጌታ አይሰጠንም፡፡ ቃሉን እራስህ በማንበብ ፈንታ ሁሌም የሌሎችን ስብከትና ምልከታ የምታሳድድ ከሆንክ ሥር መስደድ አትችልም፡፡
ያለቅጥ መቸኮል፣ የዛሬን ድካም ለማስወገድ፣ አጭር መንገድ ተኮር የሆነ ሩጫ የኋላ የኋላ ከባድ ዋጋ ያስከፍላል፡፡
እናላችሁ ቦሌ የጫማዬ ሶል ተገንጥሎ ሲወድቅ ራሴን ኮነንኩኝ፣ ለዘመናት የማልረሳውን ትምህርት ተማርኩኝ፤ ግን ምን ተጫምቼ ወደ ብርዳማው አገር ልብረር? ኤር ፖርት ያሉት ሱቆች ዋጋ፣ አይደለም በኔ አቅም በሌላውም በጭንቅ የሚቻል ነው፤ ብዙ ዶላር ደግሞ አልነበረኝም፣ ከየትስ ይመጣል? ግን ደግሞ አማራጭ አልነበረኝም፤ ከቆጠብኳት ዶላር ላይ 35ቷን አውጥቼ ከቆዳ የሚሰራ ክፍት የአገር ውስጥ ጫማ ገዛሁኝ፣ ጥቁር አንበሳ አካባቢ ባሉት ሱቆች ምናልባትም 150 ብር ያወጣ ይሆናል፣ አቤት እንዴት በራሴ እንደተናደድኩ! ያኔ በነበረው የዶላር/ብር ስሌት 500 ብር ገደማ ነው ያወጣሁት፣ ከመርካቶ ሁለት ደህና ጫማ ይገዛልኝ ነበር እኮ! እቆጥብ ብሎ እንዲህም መክሰር አለ፣ አተርፍ ብሎ ማጉደል አለ፡፡ አርቆ አለማሰብ አላስፈላጊ ዋጋ ያስከፍላል፡፡
የሰዎችን የበሰለ ማንነት አይተን እንቀናለን ግን በአንድ ጀንበር የሚሰራ ሕይወት እንደሌለ ማን በነገረን፤ ወጥ ስንሰራ ወጋ አድርጎ እንዲያበስልልን የከሰል እሳት እንመርጥ የለ? እንደጣዱ ለማውረድ መቸኮል ምንድነው? ያለ መታገስ ዕድገት የለም፡፡ አንድ ህጻን አበባ ተከለና ቀኑን ሙሉ እየተመላለሰ ሲያየው፣ ውኃ ሲያጠጣው፣ ሲኮተኩተው ዋለና አመሻሹ ላይ ነቅሎ ጣለው፤ አባት ከሥራ ሲመጣ “የታለ ጠዋት የተከልከው አበባ?” ልጅ፡- “ነቀልኩት” “ለምን?” “እንዴ! አያድግማ፤ ውኃ አጠጣሁት ኮተኮትኩት ከዚህ በላይ ምን ላርገው ታዲያ?” እንደ ህጻን እያሰብን ነው እንዴ ተስፋ የምንቆርጠው? አትሳቱ! ፈጣን (instant) ቡና፣ ፈጣን ኢንዶሚ፣ ወዘተ አሉ፣ ፈጣን የአካልም ሆነ የሕይወት ዕድገት ግን የለም፡፡ “ጌታ አዲስ ነገር ያደርጋል” ሲሉን ነባሩን በቃሉ የመታነጽን ድስፕሊን ዘመን ያለፈበት አርገን ቆጠርነው ይሆን?
ውድ ተመራቂዎች፣ እንኳን ደስ ያላችሁ! ግና ልብ በሉ፣ ፈጣን ዕድገትና አዲስ የማደጊያ ዘዴ የለም፤ ምትኃታዊ የሕይወት ለውጥም አይመጣም፡፡ ክርስቶስ አልተቀየረም፣ አሰራሩም ያው ነው፡፡ ጨክኑና፣ ሥጋችሁን በጥርሳችሁ ያዙና እግዚአብሔርን ለመምሰል ራሳችሁን አስለምዱ፣ አቋራጭ መንገድ የለውምና፡፡
የጸጋም ሁሉ አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል፣ አሜን (1ኛ ጴጥ 5፡10-11)፡፡
ዶ/ር ሰብለወንጌል ዳንኤል – የሦስት ልጆች እናትና የቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሲሆኑ በኤግስት (Ethiopian Graduate School of Theology) የሥነ መለኮት፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክና ‘የሚሽንስ’ አስተማሪ ናቸው፡፡