ባለ አደራነት
አስጢፋኖስ ገድሉ
እንደ መግቢያ
አደራ በማኅበረሰባችን መስተጋብር ውስጥ ለየት ያለ ትኩረት ከሚሰጣቸው እሴቶች መካከል አንዱ ነው….ይህ ይበል የሚያሰኝ ነው! የተሰጠውን አደራ በሚገባ ያልተወጣ ሰው “አደራውን የበላ” ተብሎ ይወቀሳል….በዚህም ኀፍረት ይሰማዋል፡፡ ይህንንም ወቀሳ ፍራቻ ጭምር ሰዎች በአደራ የተሰጣቸውን ጉዳይ በጥንቃቄ ሲይዙና ሲንከባከቡ ይስተዋላል፡፡ የኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት ባለ አደራነትን ሲተረጉም “አንድን ነገር በጥንቃቄ መከወን ወይም ማስተዳደር ለምሳሌም፡- ንብረትን፣ ተቋምን፣ ገንዘብን ወይም ውድ የሆኑ እቃዎችን….፡፡” [1] በማለት ይተረጉመዋል፡፡
በዚህች አጭር ጽሑፍ የምንዳስሰው ስለ መጽሐፍ ቅዱሳዊው ባለ አደራነት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ይህ ጽንሰ ሐሳብ ተጠቅሶ እናገኛለኝ፤ ከነዚህ ውስጥም፡- ባለ አደራ እንደ መጋቢ ሉቃ 16፡1፣ 1ኛ ጴጥ 4፡10 እና ኢሳ 22፡15፤ ባለ አደራ እንደ የቤት አዛዥ ዘፍ 19፡23፣ 24፡44 እና 43፡16፤ ባለ አደራነት እንደ አገልጋይ ሮሜ 16፡1፤ በ1ኛ ቆሮ 4፡1 እና ቲቶ 1፡7 ላይ ባለ አደራነት በቀጥታ ተጠቅሶ እናገኛለን፡፡ በነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የምናስተወለው የጋራ ጉዳይ “እንደ ራሴ” ሆነን በታማኝነት፣ በትጋትና በልቀት ከአደራ ሰጪው ከእግዚአብሔር የተቀበልነውን አደራ በተገቢው መንገድ መፈጸምን ሲሆን፤ በዚህ መልኩ በኃላፊነት ስሜት አደራን መወጣት ብድራት እንደሚኖረው፣ ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን ባለ አደራነት ተጠያቂነትንም ጭምር እንደሚያስከትል ያስተምሩናል፡፡
የባለደራነታችን መሠረቱ
የመጽሐፍ ቅዱሳዊው ባለ አደራነት መሠረቱ እግዚአብሔር የሁሉ ነገር ባለቤት መሆኑና እኛ ደግሞ በእርሱ ቦታ ሆነን በእርሱ ምሪት እና ጸጋ የምናስተዳድር ባለ አደራዎች መሆናችን ነው፡፡ መዝሙረኛው ዳዊት በመጽሐፉ እንዲህ ብሏል፡-“ምድርና በእርሷ ያለው ሁሉ፣ ዓለምና በውስጧ የሚኖር ሁሉ የእግዚአብሔር ነው፤”[2] የሕይወት እስትንፋሳችንን ጨምሮ፣ ሁሉን የፈጠረ – ሁሉን የሰጠን፤ የሁሉ ባለቤት እርሱ ነው፤ ክእርሱ ያልተቀበልነው አንዳች ነገር የለም፡፡ ደግሞም መፍጠር ብቻ ሳይሆን፣ ፍጥረታቱን እንደ ፈቃዱ ጠብቆ የሚያኖር፣ ሁሉን የሚያስወጣ የሚያስገባ፣ ሁሉን የሚገዛ እርሱ ነው፤ “ሰይጣን እንኳ ‹ሰይጥኖ› ለመኖር እግዚአብሔር ያስፈልገዋል” እንዲሉ፡፡ በመጨረሻም ዓለማትን ሁሉ በልጁ በክርስቶስ ኢየሱስ የሚጠቀልል – ለክብሩ የሚያደርገው እርሱ ነው፡፡ ምክንያቱም “ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጥሮአል፤ በሰማይና በምድር ያሉ፣ የሚታዩና የማይታዩ፣ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ኀይላት፣ ገዦች ቢሆኑ ወይም ባለሥልጣናት፣ ሁሉም ነገር በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል።” [3] እግዚአብሔር የሰው ልጆች እንዲባዙና ምድርን እንዲሞሉ እንዲገዙዋት፤ የባሕርን ዓሦችን፣ የሰማይን ወፎችን፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ እንዲገዙ ባርኳቸዋል።[4] በአደራ ሰጪውና በአደራ ተቀባዩ መካከል የሚኖረው ግንኙነት፡- ኃላፊነትን፣ ተጠያቂነትንና ሽልማትን(ብድራትን) የሚይዝ ሲሆን [5]፤ ከዚህ በታች እነዚህን ሦሰቱን የባለደራነት ገጽታዎችን በአጭሩ እንቃኛለን፡፡
አደራ እና ኃላፊነት
ሐዋርያው ጳውሎስ ወጣቱን ጢሞቴዎስ“የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍር ሠራተኛ ሆነህ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ፡፡”[6] በማለት በአንክሮ መክሮታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በኢየሱስ ክርስቶስ ባለው ጸጋ ከእርሱ የሰማውን … ለሌሎች ለታመኑ ሰዎች አደራ እንዲሰጥ መክሮታል፡፡ ጢሞቴዎስ የተረከበውን አደራ የሚፈጽምበትን መንገድ፡- የወታደርን፣ የስፖርት ተወዳዳሪና የገበሬን ሕይወትና ኑሮ በምሳሌነት በመጥቀስ በትጋት፣ በአትኩሮት እና ራሱን በሌላ ሥራ ሳያጠላልፍ ሕግን ጠብቆ እንዴት መኖርና ማገልገል እንደሚገባው አስረድቶታል፡፡[7] እግዚአብሔር ታማኝ አድርጎ ቆጥሮን የእርሱ የሆኑ ነገሮችን እንድናስተዳድር እርሱ በሆነው ነገር ባለ አደራ አድርጎ ሾሞናል፡፡ እንግዲህ ሁሉን የሰጠን-የሁሉ ባለቤት እርሱ ነው ካልን፤ ከእርሱ ለተቀበልነው ለየትኛውም ነገር ባለአደራዎች ሆነናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እንደ እርሱ ዓላማና ፍቃድ ልንኖር፤ ከእርሱ በአደራ የተቀበልናቸው ነገሮች ሁሉ እንደ ታማኝ ልጆቹ በኃላፊነት ልናስተዳድር ይጠበቅብናል፡፡ ጳውሎስ የተሰሎንቄ ሰዎችን “የምታደርጉትን ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉት ቈጥራችሁ በሙሉ ልባችሁ አድርጉት፤….” [8] በማለት እንዳሳሰበው፣ እኛም የተሰጠንን አደራ እንዲህ ባለ ኃላፊነት ልንወጣ ይገባል፡፡
አደራ እና ተጠያቂነት
የባለ አደራነት ሌላው ገጽታ ተጠያቂነትን ማስከተሉ ነው፡፡ አደራን የሰጠው አካል አደራውን እንዴት እንደተወጣነው ሊገመግም ባስቀመጠው ጊዜ ይመጣል፡፡ ከእግዚአብሔር የተሰጠን አደራ ከሌላው የሚለየው አደራውን የምንወጣው በእርሱ እይታ ውስጥ ሆነን እርሱ በሚሰጠን ምሪትና ጸጋ መሆኑ ነው፡፡ አደራ ሰጪው እግዚአብሔር የተቀበልነውን አደራ በምን መልኩ ልንወጣ እንደሚገባ ሁልጊዜ በቃሉና በመንፈሱ ያሳስበናል፡፡ በማቴዎስ ወንጌል 25 ጌታ ኢየሱስ በምሳሌነት የጠቀረበው ያ ‹‹ሰነፉ አገልጋይ›› የተሰጠውን አደራ በሚገባ ባለመወጣቱ ምክንያት ተጠያቂ ሲሆን እንመለከታለን፡፡ እንዲሁም የተሰጠውን አገልግሎት በላቀ መንገድ የፈጸመው ጳውሎስ የቆሮንጦስ ቤተ ክርስቲያንን አማኞችን”የእግዚአብሔር ጸጋ እንደተሰጠኝ እንደ ብልሃተኛ የአናፂ አለቃ መሠረትን መሠረትሁ፤ ሌላውም በላዩ ያንጻል፡፡ እያንዳንዱ ግን በእርሱ ላይ እንዴት እንዲያንጽ ይጠንቀቅ፡፡ … ማንም ግን በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ ቢሆን በብርም በከበረ ድንጋይም በእንጨትም በሣርም ወይም በአገዳ ቢያንጽ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል …፡፡” [9] ሲል አስጠንቅቋል፡፡ አደራ ኃላፊነትን ብቻ ሳይሆን ተጠያቂነትንም እንደሚያስከትል ከዚህ ሐሳብ እንረዳለን፡፡
አደራ እና ብድራት
እግዚአብሔር ልሁቅ አምላክ ነው፡፡ ከስነ-ፍጥረት ጀምሮ እግዚአብሔር የፈጠራቸው (የሠራቸው) ሥራዎች ሲጠኑ በአስገራሚ ልቀት እንደተሠሩ አጽናፈ አለሙ ሁሉ እማኝ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱሳችንም ከጫፍ እስከ ጫፍ ይህንኑ ይተርካል፡፡ እኛም ልጆቹ በአደራ ከእርሱ የተቀበልነውን ኃላፊነት በትጋት፣ በታማኝነትና በልቀት ልንፈጽም ይገባናል፡፡ ሽልማት ለዚህ ዐይነቱ ለላቀ አፈጻጸም የሚበረከት ስጦታ ነው፡፡ ከላይ እንዳየነው ጳውሎስ ለሽልማት የሚያበቃን የአገልግሎት አፈጻጸም ሲገልጽ “… በውድድር የሚሳተፍ ሰው፣ የውድድሩን ሕግ ጠብቆ ካልተወዳደረ የድሉን አክሊል አያገኝም። ትጉህ ገበሬም ከሰብሉ ለመጠቀም የመጀመሪያው ሊሆን ይገባዋል። እኔ የምለውን ልብ በል፤ ጌታ በሁሉም ነገር ማስተዋልን ይሰጥሃልና።”[10] በማለት ገልጾታል፡፡ እንዲሁም የምናደርገውን ነገር ሁሉ ለማን ብለን ማድረግ እንዳለብንና እንዴት ማድረግ እናዳለብን ከገለጸ በኋላ ‹‹…ከጌታ ዘንድ እንደ ብድራት የምትቀበሉት ርስት እንዳለ ታውቃላችሁና፤ የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስን ነው።” በማለት መልካም ሥራችን በእግዚአብሔር ዘንድ ብድራት እንዳለው ገልጾልናል፡፡ ይሁን እንጂ፣ አንዳንድ ጊዜ አደራችንን የምንወጣበት መንገድ ስናስተውለው… እንደው ብድራቱ ቢቀር ጠያቂ እንኳ ያለብን አይመስልም፡፡ ብዙ ያልታሰበባቸው የሚመስሉ የግብር የውጣ ውሳኔዎችና ድርጊቶች እለት እለት የምናስተውለው ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ አደራውን የሚጠይቅ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው ብድራትን የሚከፍል…አምላክ መኖሩን አውቀን የተሰጠንን አደራ ዳር ልናደርስ ይገባል፡፡
እንደ ማጠቃለያ
በምድር ላይ የምንኖርበት ዓላማና ተልእኮ አጠር ተደርጎ ሲጠቀለል እግዚአብሔርን ማወቅና እርሱ በሁሉ ዘንድ እንዲታወቅ ማድረግ ነው፡፡ ታላቁ የእግዚአብሔር ዓላማ “በዘመን ፍጻሜ ይሆን ዘንድ ያለው ሐሳቡ በሰማይም በምድርም ያሉትን ነገሮች ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሥር ለመጠቅለል ነው።” [11] ይህንን ዓላማ ለማስፈጸም የተሰጠን ተልእኮ ‹‹ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው፤››[12] የሚል ነው፡፡ ይህንን ተልእኮ(አደራ) ስንፈጽም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ እርሱ ሁል ጊዜ ከእኛ ጋር እንደሚሆን በዚሁ ክፍል ቃል ገብቶልናል፡፡ በሕይወት ዘመናችን በየምእራፉ ይህንን ታላቅ አደራ ልንፈጽምባቸው በምንችላቸው አያሌ እድሎች ውስጥ እናልፋለን፡፡ እነዚህ እድሎች ባለ አደራነታችንን የምንፈጽምባቸው መድረኮች ናቸው፡፡ ብንማር – የትምህርት ቤት መድረክ፤ ብንሠራ – የመሥሪያ ቤት መድረክ፤ ብንነግድ – የንግድ ሱቅ መድረክ ወዘተ፡፡ የምናልፍበት አውድ ይለዋወጥ እንጂ ተልእኳችን አይለዋወጥም፡፡ የምናደርጋቸውን ነገሮች በትጋት፣ በታማኝነትና በልቀት እያደረግን በዚህ ሁሉ ውስጥ በአደራ የተሰጠንን ተልእኮ እንፈጽማለን፡፡ የቤተ ክርቲያን መድረኮቻችን ባብዛኛው ለዚህ ተልእኮ (አደራ) የምንታጠቅበትና የምንበረታታበት ሥፍራ ሲሆኑ፣ የአገልግሎት መስኮቻችን ደግሞ የምንሰማራባቸው የሙያ ዘርፎችና በማኅበረሰቡ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የምናበረክታቸው አስተዋጽዎች ናቸው፡፡ “ወንጌልን ኑረው! አስፈላጊ ሲሆን ስበከው!” እንደሚባለው፡፡ ከንግግር ባለፈ ብርሐንነታችንንና ጨውነታችንን የምንገልጥባቸው እድሎች የሚገኙት ከቤተ ክርሰቲያን ይልቅ በማኅበረሰቡ ውስጥ በሚገኙ ‹‹መድረኮች›› ላይ ነው፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን ትጉህ ሠራተኝነትንና የሥራ ስነ-ምግባርን ሳይሆን እንዲሁ በድንገቴ ‹ትባረካለህ፣ ትጠረምሳለህ› በማለት በስንፍና የተለወሰ ጠባቂነትን እያበረታታቱ የሚገኙት አንዳንድ መድረኮቻችን ታርመው፣ “የእጆችህን ሥራ እባርካለሁ” እና “እስከ አለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፡፡” ያለውን ጌታ ታምነን በአደራ የተሰጠንን የ‹ታላቁ ተልዕኮ›ን አገልግሎት በምንሰማራበት የሥራ መስክ እንድንፈጽም የሚያስታጥቁንና የሚያበረታቱን ሊሆኑ ይገባል ብዬ አበቃሁ፡፡
[1] Oxford Advanced Learner’s Dictionary, 8th edition
[2] መዝሙር 24፡1
[3] ቁላስያስ 1፡16
[4] ዘፍጥረት 1፡28
[5] http://tifwe.org
[6] 2ኛጢሞ 2÷15
[7] 2ኛጢሞ 2÷1-7
[8] ተሰሎንቄ 3፡23
[9] 1ኛቆሮ 3÷10-15
[10] 2ኛጢሞ 2÷1-7
[11] ኤፌ 1፡10
[12] ማቴ 28-18-20