ታማኝ ባለአደራ
ውድ የ2008 የዩኒቨርሲቲ ክርስቲያን ተመራቂዎች፣
እንኳን ደስ አላችሁ፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በየተመደባችሁባቸው ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የሚገባችሁን የትምህርት ዝግጅት ስታደርጉ ቆይታችሁ ለመመረቅ መብቃታችሁ ደስ ያሰኛል፡፡ ከዚህ በኋላም ቀጣይ የሃገርና የወገን አደራ ተቀብላችሁ አደራውን ለመወጣት በየፊናችሁ ልትሰማሩ ነው፡፡ ከዚህ በበለጠ ደግሞ የእግዚአብሔር ባለአደራዎች በመሆናችሁ ባለ ድርብ ባለአደራዎች ናችሁ፡፡ ስለ እግዚአብሔር ባለአደራነታችሁ ትንሽ ማሳሰቢያ ላስነብባችሁ፡፡
የእግዚአብሔር አደራ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል አደራ ነዉ፡፡ ወንጌል በኢየሱሰ ክርሰቶስ በቃልና በኑሮ የተገለጸ፤ በሐዋርያት የተሰበከ የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ነው፡፡ ይህ የማዳን ሥራ ትውልድ ሁሉ ሊሰማው የሚገባ በመሆኑ ወንጌሉን የተቀበለ ሁሉ በቃል በማወጅ በኑሮ በማሳየት፤ ለሌላው የማስተላለፍ አደራ አለበት፡፡ የወንጌል አደራ፤ የከበረ፤ በጥንቃቄ የሚጠብቅ፣ ባለአደራ የሚያስፈልገው ፤ አደራውን ሰጪው እግዚአብሔር በትኩረት የሚከታተለው ሐብቱ ነው፡፡
እንግዲህ ፤
አደራው የከበረ ስለሆነ እናንተም አክብሩት፡፡ የከበረ የሚያደርገውም ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማዬ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ አምላክ የሰዉን ሥጋ ለመልበስ የፈቀደበት፤ ከዚያም የባሪያን መልክ በመውሰድ ለመስቀል ሞት የታዘዘበት መለኮታዊ ሥራ በመሆኑ፤ ደግሞም ሞቶ ሳይቀር ከመቃብር ተነሥቶ ወደ ሰማይ ያረገበት ተመልሶ እንደሚመጣ ያስታወቀበት መሆኑ ነዉ፡፡ ይህን የሚመስል ክስተት ከዚያ በፊት ያልሆነ ደግሞም የማይደገም ብቸኛ ድንቅ የመለኮት ሥራ ነዉ፡፡ በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ክርስቶስ ከስም ሁሉ በላይ የሆነ ስም የተቀዳጀበት፤ በዚህ ስም የሚያምኑ ሁሉ የሚድኑበት፤ ኃይላትና ሥልጣናት ደግሞ የተገዙለት፤ በሰማይ፣ በምድር፣ ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ ሊንበረከኩለት የተገባ መሆኑ ነዉ፡፡ በመሆኑም እናንተም ለዚህ ስም ክብር እየሰጣችሁ ለስሙም የሚመጥን ሕይወት እየኖራችሁ ክቡርነቱን ግለፁ፡፡
አደራው ታማኝ ባለአደራ ፈላጊ ስለሆነ ታማኞች ሁኑ፤ እግዚአብሔር የወንጌልን አደራ ሲሰጣችሁ የወንጌልን አደራ ለመጠበቅ ብቃት ስለአላችሁ ወይም ታማኝ ሆናችሁ ስለተገኛችሁ ሳይሆን በክርስቶስ በማመናችሁ ታማኝ አድርጎ ስለቆጠራችሁ ነዉ፡፡ “ ለአገልግሎቱ ሾሞኝ ታማኝ አድርጎ ስለ ቆጠረኝ ….. (1ጢሞ 1፤12) እንደሚል፡፡ ሰው በራሱ ይሄንን አደራ መወጣት አይችልም፡፡ “ ነገር ግን የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ዉስጥ አለን፤“ (2ቆሮ. 4፡7) ተብሎ ተጽፏል፡፡ እግዚአብሔር የራሱን ኃይል ተማምኖ እንደ ሸክላ ተሰባሪና አቅመ ቢስ በሆነ ሰው ዉስጥ የከበረውን መዝገብ አኖረ፡፡ በመሆኑም እናንተም ይሄንን ኃይል በመተማመን አደራውን ጠብቁ፡፡ ቃሉ እንደሚል “ … ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢያት አስወግደን የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ …፡፡ “ (ዕብራውያን 12፡2) ታማኝ ሆኖ ለመገኘት ታማኝ የሆነውን ክርስቶስን በመከተል፤ በማየትና በማሰብ የሕይወት ሩጫችሁን ሩጡ፡፡ ከዚህም ጋር አደራው ታማኝነታችሁን የሚቆጣጠርና የሚጠይቅ ባለቤት ስለአለው ተጠያቂ መሆናችሁን በማሰብ ተመላለሱ፤ የወንጌሉ ባለቤት እግዚአብሔር ነው፡፡
ወንጌሉን በአደራ ተቀበላችሁ እንጂ ባለቤት አይደላችሁም፡፡
ስለዚህም ተጠያቂ መሆናችሁን ግምት ውስጥ በማስገባት ኑሩ፤ በአገኛችሁት አጋጣሚ ሁሉ አገልግሉ፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ 25፡14-30 የሰጠው ትምህርት ባለአደራ ተጠያቂ እነደሆነ የሚገልጽ ምሳሌ ነዉ፡፡ በምሳሌው እንደተገለጸው አንድ ጌታ ሦስት ባሪያዎቹን ጠርቶ፤ ለባሪያዎቹ አምስት፤ ሁለትና አንድ መክሊት ሰጣቸው፡፡ ባሪያዎቹ ባለአምስቱ ነግዶ አምስት አተረፈ፤ ባለሁለቱ ነግዶ ሁለት አተረፈ፡፡ ባለአንዱ ግን መክሊቱን ወስዶ ቀበረዉ፡፡ መክሊቱን የሰጣቸው ጌታ በመጣና በተቆጣጠራቸው ጊዜ ሁሉም መልስ ሰጡ፡፡ ጌታቸውም
ነግደው ላተረፉት ሁለቱ
- መልካም፤ በጎና ታመኝ ብሎ ጠራቸው
- በጥቂቱ ስለታመኑ በብዙ እንደሚሾሙ አስታወቃቸው
- ወደ ጌታቸው ደስታ መግባትን ሰጣቸው፡፡
ላልነገደው ግን
- ክፉና ሐኬተኛ ብሎ ጠራው
- ስለእኔ ያወቅኸውን አልተገበርኸዉም አለው
- ወደ ጨለማው አውጡት አለ፡፡
በማጠቃለያውም ሲናገር ታማኝነት መጨመርን፤ መሸለምን ሲያስከትል፤ ታማኝ አለመሆን ደግሞ መጉደልን፤ ባዶነትን እንደሚያመጣና ቅጣትም እንዳለው አመለከተ፡፡ ስለሆነም በቀጣዩ ዘመናችሁ ሁሉ የትም ብትኖሩና ምንም ብትሰሩ የወንጌሉን አደራ በታማኝነት ለመወጣት ፤ በየመክሊታችሁ ነግዶ ለማትረፍ ትጉ፡፡
ታማኝነታችሁን የምትገልጡት በዋናነት
ሀ. ለወንጌሉ ይዘት ያለማሰለስ በመጠንቀቅ፤ ወንጌል ከክርሰቶስ ኢየሱስ ጤናማ ቃልና እግዚአብሔርን ለመምሰል በሚስማማ ትምህርት መሰበክ አለበት፡፡ ከዚህ የወጣ ሁሉ ሥሩ ትዕቢት ወይንም እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ ለማግኘት የሚደረግ የክብርና የገንዘብ ጥማት ስለሚሆን ከባለአደራነት ያጎድላል፡፡ ስለሆነም ወንጌልን ስትሰብኩትና ስትኖሩት በውሸት እውቀት ከመሰለ ከከንቱ መለፍለፍ በመራቅ፤ ኑሮዬ ይበቃኛል በማለት ገንዘብን ባለመውደድ ( 2ጢሞ 6፡3-10)፤ የብሩክ እግዚአብሔርን ክብር በሚገልጥ መንገድ ይሁን፡፡ (2ጢሞ 1፡11)
ለ. ቃሉን በጠበቀ መንገድ ያለ እድፍና ያለ ነቀፋ ሆኖ በመመላለስ፤ የክርሰቶስ ወንጌል የሚነገር የሚዲያ ሪፖረት ሳይሆን በሕይወት የሚገለጥ እዉነት ነዉ፡፡ በመሆኑም እንደወንጌሉ ቃል ኑሩ፤ ተናገሩ፤ ሥሩ፡፡
ሐ. ለታመኑ ሰዎች በማስተላለፍ ፤ ወንጌል ወደ እኛ የደረሰዉ በቅብብሎሽ ነዉና ለማቀበል አነጣጥሩ፤ በጊዜዉ ደግሞ አቀብሉ፡፡
መ. መከራን ለመቀበል በመፍቀድ፤ ወንጌልና መከራ አይለያዩም፡፡ ወንጌል ስንኖረዉም ስናዉጀዉም በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ መከራን መቀበል አይቀሬ ነዉ፡፡ ይህ ስለክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና ስለእርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፡፡ “ በእዉነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ፡፡ “ ( 2ጢሞ 3፡12) የሚለዉን ቃል አትዘንጉ፡፡ ምንም ጊዜ ቢሆን በማያሳፍረዉ ወንጌል ሳታፍሩ ስለወንጌሉ መከራን ለመቀበል የተዘጋጃችሁ ሁኑ፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ታማኝ ባለአደራዎች እንድትሆኑ ይርዳችሁ
በጌታ እህታችሁ
ጥሩወርቅ መስፍን