እንኳን ደስ አላችሁ!
መጨረስ ደስ ይላል! “ከነሙሉ ክብሩ፣ ጥቅሙና ግዴታው ጋር!” እንዲሉ፤ ይህ ዓይነቱ መጨረስ የሌላ አዲስ ምዕራፍ ጅማሬ እንጂ በራሱ የሁሉ ነገር ፍጻሜ አይደለም፡፡ በትምህርት ቤት ቆይታችን የሰበሰብናቸው ነገሮች፣ ወደፊት በምንሰማራበት የሥራ መስክ በተሻለ መልኩ ለሰዎች በረከትን፣ ለእግዚአብሔር ደግሞ ክብርን የምናመጣበት የአገልግሎት ዕድልን ያሰፋልናል፡፡ በተለይ ይህ ወቅት ምን አገኛለሁ በሚል ስሌት ብቻ ሳይሆን ምን አስተዋጽዎ አደረጋለሁ በሚል ልብ ራሳችንን ለተሻለ አገልግሎት የምንዘጋጅበት ጊዜ ሊሆን ይገባል፡፡ በዚህ በዘመናችን ቤተ ክርስቲያን እና አገርን እየተፈታተኑ ያሉ ልዩ ልዩ ተግዳሮቶችን ከመፍታት አንጻር ከእኛ ትውልድ ብዙ ይጠበቃል፡፡ እንግዲህ በቀረው ዘመናችሁ በምታልፉባቸው የሕይወት ምእራፎች ሁሉ የሁልጊዜ ጥማታችሁ እና ተልዕኮዋችሁ እግዚብአሔርን ማወቅ እና እርሱን ማሳወቅ እንዲሆን ምኞቴና ጸሎቴ ነው፤ ይህ፣ በምድር ላይ የመኖራችን ዓላማና ዘላለማዊ ደስታን የሚሰጠን ተግባር ነውና!
እስጢፋኖስ ገድሉ፣
የኢንዱሰትሪ ቴክኖሎጂ ምሩቅ፣ መቐሌ ዩኒቨርሲቲ