በኢቫሱ የተማሪዎች አገልግሎት በተደጋጋሚ ከምንወስዳቸው ስልጠናዎች አንዱ ‹ከቃሉ ጋር መገናኘት› (Scripture Engagement) የምንለው ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ከቃሉ ጋር ይበልጥ ለመገናኘት ልባችንን የሚያነሳሱ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን እናያለን፡፡ ይህንኑ ሃሳብ በሶስት ንዑሳን ሐሳቦች ከፍለን እናየዋለን፤ ቃሉና እግዚአብሔርን መውደድ፣ ቃሉና የሕይወት ተሃድሶ እና ቃሉና የመንግስቱን ወንጌል መረዳት የሚሉ ናቸው፡፡
ቃሉና እግዚአብሔርን መውደድ (ዘዳ 6፡1-9)
በዚህ ክፍል ከቁ.1-3 ያሉትን ሐሳቦች ስናይ የእግዚአብሔር ትእዛዛት ለሕዝቡ የተላኩበትን ዓላማ ሙሴ ያሳስባቸዋል፡፡ ይኸውም ዕድሜህ እንዲረዝም (ቁ.2)፣ መልካም እንዲሆንልህ (ቁ.3)፣ እና እጅግ እንድትበዛ (ቁ.3) በማለት በብሉይ ቃል ኪዳን ቋንቋ ይገልጸዋል፡፡ በመቀጠል ሙሴ ወደ ዋናው የትዕዛዛቱ ትንተና ሲገባ የሚጀምርበት የመጀመሪያው ሃሳብ እግዚአብሔርን ውደድ (ቁ.5) የሚል ነው፡፡ እርሱ ደግሞ የሚወደደው እንዴት እንደሆነ ሲገልጽ በፍጹም ልብ፣ በፍጹም ነፍስ፣ በፍጹም ኃይል እንደሆነ ይገልጻል (ቁ.5)፡፡ (ክርስቶስ ኢየሱስ በማር12፡30 ላይ ‹በፍጹም ሃሳብህ› የሚል አራተኛ ሃሳብ ጨምሮበታል) አራቱም ቃላት በሁለንተናዊ ማንነታችን፣ በፈቃዳችን፣ በእውቀታችን፣ በስሜታችን እግዚአብሔርን መውደድ እንዳለብን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ ከዚህ በመቀጠል ‹እኔ ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ› ይላል (ቁ.6)፡፡ ቃሉን በልብህ ያዝ ከማለቱ በፊት አምላክህን ውደድ ብሏል፡፡ የማንወደውን አካል ቃል፣ ሃሳብ፣ ትዕዛዝ፣ ትምህርት በልባችን መያዝ አንችልም፡፡ ሰው የማይወደው ነገር በአእምሮው አይያዝለትም፡፡
እርሱ መጀመሪያ በመስቀል መስዋዕትነት ወዶናልና በምላሹ እንወደዋለን፡፡ ከአምላካችን ጋር ያለንና የሚኖረን የፍቅር ግንኙነት የሚጀምረው መስቀሉ ጋር ነው፡፡ የፍቅር ግንኙነት ከጀመርን በኋላ የምንመጣው (መምጣት ያለብን) ወደ ቃሉ ነው፡፡ ስለዚህ የፍቅር ግንኙነታችን በተለያየ መንገድ በምንሰማው የወንጌል ቃልና፣ በምናየው የወንጌል ሕይወት ምስክርነት ይጀምርና፣ እያደገና እየጎለበተ የሚሄደው፣ አምላካችንን በቃሉ አማካኝነት መገናኘት፣ መተዋወቅ፣ መታዘዝ፣ መከተል፣ ማገልገል ስንጀምር ነው፡፡
ስለዚህ በዚህ ባለንበት ዘመን፣ በተከሰተው ወረርሽኝ ምክንያት፣ በቤታችን ለመሆን ባገኘነው ረጅም ጊዜ ተጠቅመን፣ ለምን ከአምላካችን ጋር በቃሉ በኩል ግንኙነታችንን፣ ኅብረታችንን፣ ፍቅራችንን አናሳድግም?
ቃሉና የሕይወት ተሃድሶ (ነህ 8 – 9፡4)
በነህምያ ምዕራፍ 8 ላይ የምናየው ነህምያ ከፋርስ መጥቶ፣ የፈረሰው የኢየሩሳሌም ቅጥር በ52 ቀናት ውስጥ ተገንብቶ ካለቀ በኋላ የሆነውን ነገር ነው፡፡ በሰባተኛው ወር የመጀመሪያው ቀን ሕዝቡ ሁሉ እንደ አንድ ሰው ሆነው ተሰብስበው ወደ እዝራ በመምጣት የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ ያመጣ ዘንድ ነገሩት(ቁ.1)፡፡ እርሱም የሕጉን መጽሐፍ አምጥቶ ሊያነብ በገለጠው ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ቆሙ (ቁ.5)፡፡ መጽሐፉንም ከማንበቡ በፊት እግዚአብሔርን ባረከ፤ ሕዝቡም አሜን በማለትና በመስገድ ለእግዚአብሔርና ለቃሉ ያላቸውን አክብሮት ገለጹ (ቁ.6)፡፡ በዚህም ቀን እዝራ ለግማሽ ቀን ያህል የሕጉን ቃል አነበበ፤ ሕዝቡም ያደምጥ ነበር (ቁ.3)፡፡ ከቃሉም ጋር በዚህ መልክ የመገናኘታቸው ዓላማ እግዚአብሔርን ለማወቅ ነበር (ቁ.8)፡፡ ሕዝቡም የሚነበበውን ቃል ያስተውሉ እንደነበር በቁ.3 እና በቁ.12 ላይ ተገልጿል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ከቃሉ ጋር የመገናኘት ጊዜም ከሰባተኛው ወር የመጀመሪያ ቀን አንስቶ እስከ ስምንተኛው ቀን እንዳደረጉ ተጽፏል (ቁ.18)፡፡
እንዲህ ዓይነቱ ከቃሉ ጋር የሚሆን ግንኙነት በሕዝቡ ላይ ምን ለውጥ አመጣ ብለን ስናስብ የሚከተሉትን ነገሮች እናያለን፡፡ የመጀመሪያው በሚነበበው ቃል ውስጥ ሕይወታቸውን ማየት ስለቻሉ ወደ ትክክለኛው ሃዘንና ንስሐ አምጥቷቸዋል (ቁ.9-11፣ 9፡3)፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ቃሉን ካለማንበባቸው የተነሳ፣ እግዚአብሔር እንዲደረጉ አዝዞ፣ በእነርሱ አለማወቅ ሳይደረጉ ቀርተው የነበሩ ነገሮችን ወደ ማድረግ አምጥቷቸዋል (ቁ.13-15)፡፡ ስለዚህ ትልቅ የሕይወት ተሃድሶ ጅማሬ ሆነላቸው፡፡
እኛስ ዛሬ ባገኘነው ጊዜ ከቃሉ ጋር (በቃሉም አማካኝነት ከአምላካችን ጋር) በትክክልና በሚፈለገው መጠን መገናኘት ብንጀምር ታላቅ የሕይወት ተሃድሶ አይሆንልንምን?
ቃሉና የመንግሥቱን ወንጌል መረዳት (ሉቃ 24፡13-47)
በዚህ ክፍል ላይ ጌታ ኢየሱስ ከሞት በተነሳበት ቀን ሁለት ደቀመዛሙርት ከኢየሩሳሌም 11 ኪሜ ያህል ወደምትርቅ ኤማሁስ ወደምትባል መንደር ሲሄዱ እንመለከታለን፡፡ አካሄዳቸውም በመጠውለግና በሃዘን እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ለእስራኤል ፖለቲካዊ ነጻነት ያመጣል ብለው የታመኑበት ነብይ ተገድሏል፡፡ በዚሁ ጉዞ በጀመሩበት ቀን ማለዳ ደግሞ ወደ መቃብር የሄዱ ሴቶች ‹ተነስቷል› የሚል ዜና ቢያመጡም አላመኑም፡፡ ይህንኑ እየተነጋገሩ ሲሄዱ ጌታ ኢየሱስ በመንገድ ላይ አብሯቸው መጓዝ ይጀምራል፡፡ ስለ ምን እንደሚነጋገሩም ጠይቆ በሰጡት መልስ መንደርደሪያነት፣ በሙሴና በነብያት መጻሕፍት ስለ ክርስቶስ መከራ መቀበልና መነሳት ወደ ተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይመልሳቸዋል (ዘዳ 18፡15-19፣ መዝ (16)፡9-11፣ መዝ (22)፣ ኢሳ 53)፡፡ ከቃሉ ጋር አገናኛቸው፤ ተረጎመላቸው (ቁ.27)፡፡ የተጻፈውን አለማስተዋላቸውንና አለማመናቸውንም ይወቅሳል (ቁ.25-27)፡፡
ዓይናቸው ተከፍቶ እርሱ እንደነበር ካወቁ በኋላም፣ በዚያው ምሽት ያን ሁሉ መንገድ ተጉዘው በመመለስ፣ ወደ ኢየሩሳሌም አሥራ ሁለቱ በር ዘግተው ወደ ተቀመጡበት ይመለሳሉ፡፡ እዚያም ደርሰው ቀኑን የገጠማቸውን ነገር በመመስከር ላይ እያሉ ጌታ ኢየሱስ ራሱን ይገልጣል፡፡ በዚያም የተሰበሰቡት ከሞት መነሳቱን ማመን ስላልቻሉ በተለያዩ መንገዶች ሊያሳያቸው ከሞከረ በኋላ ያመጣቸው ወደ ቃሉ ነው (ቁ.41)፡፡ ከመሞቱ በፊት ከእነርሱ ጋር እያለ እንዴት ከኦሪት፣ ከነቢያት እና ከመዝሙር መጻሕፍት እየጠቀሰ ስለ መሞቱና መነሳቱ አስፈላጊነት ይነግራቸው እንደነበረ አስታወሳቸው (ቁ.44)፡፡ በተጨማሪም ይህንኑ መሠረታዊ የእግዚአብሔር መንግሥት ወንጌል ሃሳብ ከቃሉ መረዳት እንዲችሉ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው (ቁ.45)፡፡
እኛም ከቃሉ ጋር በመገናኘት፣ ከእርሱ ጋር ለመገናኘት ስንቀርብና፣ እርሱ ደግሞ ቃሉን መረዳት እንድንችል አእምሮአችንን ሲከፍትልን፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል በሙላት እየተረዳን እንመጣለን፡፡
ስለዚህ አሁን ያገኘነውን ጊዜ፣ ለዚህ ታላቅ ዓላማ፣ ከቃሉ ጋር ለመገናኘት ልንጠቀምበት ያስፈልጋል፡፡
እግዚአብሔር ይረዳናል፤ እንነሳና ቃሉን ለማንበብ እንግለጥ፡፡
Author: Mesay Imiru, Associate of EvaSUE