ወንጌል አድራሹ ሰው፣ መልእክቱን ለማድረስ…
የወንጌል የምሥራች የሰውን የዘላለም እጣ ፈንታ የሚወስን ታላቅ መልእክት ነው፡፡ ይሄን ለዘላለም ድኅነት የሆነውን የምሥራች ሊሰሙት የተገባቸው ደግሞ የሰው ልጆች ሁሉ ናቸው፡፡ የምሥራቹ አዋጅ የሚታወጅበት ሥፍራም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ነው፡፡ የዘላለም ህይወት አዋጁን የሚናገሩት ደግሞ በወንጌሉ አምነው የዳኑ ቅዱሳን ሁሉ ናቸው፤የወንጌልን የምሥራች ለህዝብ ሁሉ እንዲናገሩ ተልዕኮን ተቀብለዋል፡፡ የሚናገሩት የወንጌል መልዕክት እስትንፋሰ እግዚአብሔር በሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ አማኞች፣ የምሥራቹን የሚናገሩበትን ሥልጣን፣ ተልዕኮውን ከሰጣቸው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተቀበሉም ከቅዱስ ቃሉ መረዳት ይቻላል፡፡ የሚናገሩት የምሥራች ህያው ነው፤ ለማዳንም ሃይል አለው፡፡
በወንጌል ምስክርነት ተግባር ላይ መስካሪው( ሰው) እና ምስክርነቱ (አዋጁ) በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ሁለቱም ነገሮች ለውጤታማ ምስክርነት ወሳኝ ናቸው፡፡ መስካሪው ሰው፣ ከሚመሰከረው ቃል ጋር የሰመረ ጥምረት ሊኖረው ያስፈልጋል፡፡ ጥምረቱ ባልሰመረ ጊዜ ሁሉ ግን፣ የወንጌል አደራን ከመወጣት ጋር በተገናኘ ብዙ ተግዳሮቶች ይገጥሙናል፡፡ ከምስክርነቱ ጋር በተያያዘ፣ ሰዎች ትክክለኛውን የወንጌል መልዕክት ማስተላለፍ ሣይችሉ መቅረት አንዱ ነው፡፡ ወንጌሉን ከምድራዊ ነገሮች ጋር ብቻ ማያያዝና በወንጌል ከማመን ጋር ተያይዞ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ተስፋን መስጠት ብዙ ጊዜ የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው፡፡ በመስቀል ላይ በክርስቶስ ኢየሱስ የተሠራውን የድኅነት ሥራ ሣይቀንሱ፤ሣይጨምሩ መናገር አለመቻል ይስተዋላል፡፡
ሌላው ተያያዥ ችግር ምስክርነቱን ከሚሰጠው ሰው ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ወንጌልን በተሣሣተ ትኩረት የማቅረብ ችግር ይስተዋላል፡፡ የምሥራቹን መልእክት ባለማወቅ መርዶ ያደርጉታል፡፡ ከዚህ የተነሣ ሣይታወቀን የምስራች አብሣሪዎች ሣንሆን ፍርድን ተናጋሪዎች ሆነን እንገኛለን፡፡ ከዘላለም ሞት ትድናለህ ከማለት ይልቅ ትሞታለህ ማለት የሚቀናቸው አማኞች ጥቂት አይደሉም፡፡ የምሥራቹን ሰምተው ላለመቀበል ልባቸውን ያደነደኑ ሰዎች ፍርድ እንደሚጠብቃቸው ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን የወንጌል አዋጅ ከትሞታለህ አይጀመርም፡፡ ወንጌል በፍቅር የሚነገር ለሰሚው የምሥራች የሆነ መልእክት ነው፡፡
ወንጌል መስካሪው፣ መልዕክቱን የሚያቀርብበት መንገድ አመቺነት ሌላው ከግምት ውስጥ መግባት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ይሄ የስልት ጥያቄ ነው፡፡ ወንጌል ተናጋሪው ሰው፣ መልዕክቱን በእንዴት ያለ ሁኔታ ብናገረው ውጤታማ እሆናለሁ ብሎ መጠየቅ ይገባዋል፡፡ ወንጌል አድራሹ ሰው፣ መልዕክቱን ለማድረስ የሚያስችለውን ውጤታማ የሆነ መንገድ (ስልት) የመምረጥ ሃላፊነት አለበት፡፡