ውድ ተመራቂዎች ከሁሉ አስቀድሜ በህይወት ዘመናችሁ ከሚያጋጥሟችሁ ጥቂት አስደሳች እና የአዲስ ምዕራፍ ጅማሬ የሆኑ ወቅቶች መካከል አንድ ለሆነው የምረቃ በኣላችሁ እንኳን አበቃችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡
በእውነትም ለዓመታት በትምህርት ገበታ የሚያጋጥሙ የክፍል ውስጥ እና ከክፍል ውጪ ያሉ ፈተናዎችን ብሎም ለአብዛኛዎቻችሁ በአዲሱ እራስን የመቻል እና በእግር ለመቆም የመፍጨርጨር ትግል አሸንፋችሁ በድል በመመረቃችሁ ደስ ሊላችሁ ይገባል፡፡ በተለይም ደግሞ እንደ ኢቫሱ ባሉ ተማሪዎችን ለማገዝ ከአብያተ ክርስቲናት ጎን የተሰለፉ ተቋማት ያመቻቹላችሁን እድል በመጠቀም በልዩ ልዩ የተማሪዎች ኅብረቶች ውስጥ በመታቀፍ አገልግሎት ስታበረክቱና ስትገለገሉ ቆይታችኋል፡፡ ያለፉት ዓመታት ዝግጅቶቻችሁ ምድራዊ እውቀት በማግኘት ላይ ብቻ ያተኮሩ ሳይሆኑ በመንፈሳዊ ሕይወትም አድጋችሁ በሁለንተናዊ መልኩ ሙሉ ሰው ወደ መሆን አድጋችሁ የሥራና የአገልግሎቱን ዓለም የምትቀላቀሉ የሚያደርጋችሁ እንደነበር አምናለሁ፡፡ ስለዚህ፣ ቆይታችሁ ከእናንተም ባሻገር በእናንተ ህይወት ላይ ጉልበታቸውን ጸሎታቸውን እና ጊዜያቸውን ያፈሰሱ አብያተክርስቲያናት፣ ቤተሰቦቻችሁን እና ሌሎች አጋሮቻችሁን ሁሉ የሚያስደስት ነው፡፡
በዚህ ዘመን እግዚአብሔር መልካም እድልን ፈጥሮ በብዙ አቅጣጫ ሁለንተናዊ እድገትን እንድትቀስሙ ማድረጉ ለራሱ ዘላለማዊ ዓላማ ማስፈጸሚያ ሊያደርጋችሁ እያዘጋጃችሁ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይህንንም መጽሐፍ ቅዱሳችን በተደጋጋሚ በብዙ የእምነት አርበኞች ህይወት ሲፈጽመው ታይቷል፡፡ አስቴር ለምድራዊ ንግስትነት ተመርጣ ቤተመንግስት ብትገባም ለእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ ከጅምላ ጭፍጨፋ መትረፍ ምክንያት ሆናለች፡፡ ዳንኤል ታላቅ የእግዚአብሔር ነቢይ ቢሆንም በዘመኑ የበርካታ ገናና ነገስታት አማካሪ ታላቅ ባለስልጣንም ነበር፡፡
ውድ ምሩቃን፣ እናንተም እግዚአብሔር በምድራዊ እና በመንፈሳዊ እውቀት አስታጥቆ በመላ አገሪቱ ወደ ሚገኙ ልዩ ልዩ የአገልግሎት ዘርፎች ሲያሰማራችሁ ዘላለማዊ አጀንዳውን እንድታስፈጽሙ መመረጣችሁን ለአፍታም ሳትዘነጉ ልትፈጽሙት ይገባል፡፡ ለዚህም በሄዳችሁበት ሁሉ የታላቁ ተልዕኮ አደራን ለመወጣት እናንተን ያፈሩ ቤተክርስቲናያት የሁል ጊዜ አገልጋዮች ልትሆኑ ባገኛችሁት እውቀት ሁሉም ልታገለግሉአቸው ታማኝ ልትሆኑ ይገባችኋል፡፡ እናንተ በሄዳችሁበት ስፍራ ሁሉ የምትኖሩት ህይወት በአሉታዊም ሆነ በአወንታዊ መልኩ እናንተን ያሳደጉ እና ለዚህ ያበቁ ቤተክርስቲያናት ስም አብሮ እንዲነሳ ያደርጋል፡፡ ስለሆነም በመንገዳችሁ ሁሉ እግዚአብሔር ወዶ እና ፈቅዶ በእናንተ ህይወት ያፈሰሰው መልካም መንፈሳዊ ወተት ከህይወታችሁ እየፈለቀ ብዙዎችን የተጠሙትን ሊያረሰርስ ይገባል፡፡ ሁልጊዜ በምትደርሱበት ስፍራ ሁሉ ታማኝ የክርስቶስ ደቀመዛሙርት እና ያሳደገቻችሁ ቤተክርስቲያን ታማኝ አገልጋይ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ይርዳችሁ፡፡
እኔ ዛሬ ለእናንተ የምክር ቃል ለማስተላለፍ የደፈርኩት ወንድማችሁ ልክ እንደእናተው ሁሉ በዩኒቨርሲቲ ተማሪነት እና በተማሪዎች ኅብረት አገልጋይ በመሆን አሳልፌያለሁ፡፡ እናም ዛሬ የደረስኩበት ይህይወት ምዕራፍ ላይ ቆም ብዬ ሳይ እግዚአብሔር እነዛን የተማሪነት እና የክርስቲያን ተማሪዎች ኅብረት አካል የሆንኩባቸውን ዘመናት እንዴት እኔን ለላቀ አገልግሎት ለማዘጋጀት እንደተጠቀመባቸው በማስታወስ አመሰግነዋለሁ፡፡ እናንተም እግዚአብሔር የፈጠረላችሁን በር ሁሉ ተጠቅማችሁ የክርስቶስ ደቀመዛሙርት እንደመሆናችሁ በምትደርሱበት ሁሉ ጌታን በህይወታችሁም ሆነ በቤተክርስቲያን የወንጌል አገልግሎት በመሳተፍ አሳዩ፡፡ ታማኙ አምላካችሁ ለኔ እንዳደረገው በየሄድኩበት ሁሉ የአገልግሎት ዱካ እንድተው ከዚያም በአገር አቀፍ ደረጃ በአገራችን ትልቋ የሆነችውን የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን በፕሬዘዳንትነት እንድመራ አብቅቶኛል፡፡
ውድ ምሩቃን፣ ከዚህም ባሻገር ክርስቲያን ባለሙያ (professional) በሙያው የተመሰገነ እና ለሌሎች አርአያ ሊሆን ይገባዋል፡፡ እናንተም ልክ እንደዚሁ በምትደርሱበት ሁሉ የትጋት አብነቶች እና በዙሪያችሁ አብረው ለሚሠሩ ሁሉ በረከት ልትሆኑ ይገባችኋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ሁል ጊዜ እራሳችሁን በእውቀት፣ በልምድ፣ እና በብቃት ለማሳደግ ትጉሃን ልትሆኑ ይገባችኋል፡፡ ይህንን ስል ግን በዚህ ዘመን እግዚአብሔርን የማይፈሩ ሰዎች እንደሚያደርጉት በሰዎች ጫንቃ ላይ ለሰዎች የሚገባውን እድል በመመንተፍ ለራስ ብቻ በማሰብ አገርን እና ወገንን ችላ ብሎ በመራመድ የሚገኝ እድገትን ከመመኘት እና ለማግኘት ከመጣር እንድትቆጠቡም ላስታውሳችሁ እወዳለሁ፡፡
በድጋሚ እንኳን እግዚአብሔር ረዳችሁ፤ ለዚህ አበቃችሁ እያልኩ መጻኢ የህይወት ዘመናችሁ ብሩህ እንዲሆን መልካም ምኞቴን ልገልጽላችሁ እወዳለሁ፡፡
ፕ/ር ተከተል ዮሐንስ
የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲን የቀድሞ ፕሬዘዳንት