በኢትዮጵያ ወንጌላውያን ክርስቲያን ተማሪዎችና ምሩቃን ማሕበር ( ኢቫሱ)፣ የሚዘጋጀው ዓመታዊው የዩኒቨርሲቲና ኮሌጅ ወንጌላውያን ክርስቲያን ተማሪዎች ሕብረቶች፣ የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ ይጀመራል፡፡
ብሔራዊ ጉባኤው፣ ከ አንድ መቶ ሃምሣ ስምንት (158) የመንግስትና የግል ዩኒቨርሲቲና ኮሌጅ የክርስቲያን ተማሪዎች ሕብረቶች የሚወከሉ የተማሪ መሪዎች የሚሣተፉበት ሲሆን፣ የተሣታፊዎቹ ቁጥርም አምስት መቶ (500) እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡
በዚህ ዓመት፣ የጉባኤው መሪ ሐሳብ ፣ በካምፓስ ውስጥ ኢየሱስን እየመሰሉ መኖርና መመስከር የሚል ነው፡፡ የክርስቲያን ተማሪዎች ሕብረቶች፣ ኢየሱስ ክርስቶስን በመምስል ህይወት እንዲያድጉ፤ የእሱንም ተልእኮ በመፈፀም እንዲተጉ የሚያግዙ ስልጠናዎችን መስጠት የፕሮግራሙ ዋና አካል ይሆናል፡፡ በዚህ ጉባኤ፣ የተማሪ መሪዎች እርስ በርስ ልምድ ይለዋወጡበታል፤ አንዳቸው ስለሌላቸው አገልግሎት ሸክምን ይጋሩበታል፣ ወዳጅነትንም ያጠነክሩበታል፡፡ በተጨማሪም ጉባኤው፣ ከተማሪዎች አገልግሎት ጋር የተያያዙ ምክክሮች የሚካሄድበት፣ ልዩ ልዩ ውሳኔዎች የሚተላለፍበትም እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ጉባኤው የሚካሄደው ቢሾፍቱ(ደብረዘይት) በሚገኘው የመሠረተ ክርስቶስ ሥነ-መለኮት ኮሌጅ ሲሆን፣ ከዛሬ ሰኞ ( ነሐሴ 8/12/2009 ዓ.ም) ጀምሮ እስከ እሑድ (ነሐሴ 14/12/2009 ዓ.ም) ይቆያል፡፡