የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ተማሪዎችና ምሩቃን ማኅበር (ኢቫሱ)፣ ለቤተክርስቲያን መሪዎችና አጋር አካላት ያዘጋጀው የአንድ (1) ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ የውይይት መድረክ ባለፈው የካቲት 15 /2010 ዓ.ም በሳሮ-ማሪያ ሆቴል ተካሂዷል፡፡
ኢቫሱ፣ የቤተክርስቲያን አጋዥ ተቋም ነው፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ፣ በከፍተኛ ተቋማት የሚገኙትን የወንጌላውያን ክርስቲያን ተማሪዎች ሕብረቶችን እያገለገለ የሚገኘው፣ ይኸው ተቋም(ኢቫሱ)፣ ከተመሰረተ ሃምሳ ሦስት ዓመት ሆኖታል፡፡ ወንጌላውያን ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ተገቢውን መንፈሳዊ አገልግሎት አግኝተው ወደመጡበት አጥቢያ ቤ/ክ እንዲመለሱ ይሠራል፡፡ተቋሙ፣ የቤተክርስቲያን አጋር፣የስራውም ባለ አደራ እንደመሆኑ የሚሠራውን ሥራ ለቤተእምነቶችና አጋር ለሆኑት መንፈሣዊ ተቋማት ማሣወቅና በስራው ውስጥ ገንቢ በሆነ መልኩ ማሣተፍ እንዳለበት ያምናል፡፡ ይህን ሥራ እስካሁን ድረስ በልዩ ልዩ መንገዶች ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን፣ አሰራሩ ወጥነትና ቀጣይነት ያልነበረው በመሆኑ በትብብር በመስራት ሊገኝ የሚችለውን ውጤት የተፈለገውን ያክል እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ ይሄኛው መድረክ፣ የቀደሙ ክፍተቶችን ለመሙላት፣ ለበላጭ ውጤትም ለመትጋት እንደሚረዳ ታምኖበት የተዘጋጀ ነው፡፡ በተጨማሪም፣ የካምፓስ ወንጌላውያን ተማሪዎች አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ መስፋትና የአብያተክርስቲያናት ቁጥር መጨመር፣ ይህ የግንዛቤ ማስጨበጫና የውይይት መድረክ እንዲዘጋጅ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
የሚከተሉት ጉዳዮችም የመድረኩ አስፈላጊነት ተጨማሪ ማሣያ ነበሩ፡-
-
አንዳንድ ቤተ-እምነቶች (በተለይ አዳዲስ የሆኑት) እና የቤተ-እምነት መሪዎች ስለ ኢቫሱ አገልግሎት በቂ ግንዛቤ የሌላቸው መሆኑ፡፡
-
አንዳንድ ቤተ-እምነቶች ስለ ኢቫሱ የሚያውቁት ነገር ቢኖርም፣ ወቅታዊ ስለሆነው ተቋማዊ አሠራርና አገልግሎት በቂ ግንዛቤ አለመያዛቸው፡፡
-
የኢቫሱ አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ በመምጣቱ፣ ቤተ-እምነቶችን በሥራው ውስጥ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ማሣተፍ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ፡፡
-
ቀጣይ የኢቫሱ – ቤተክርስቲያን አጋርነትን በአስተማማኝ መሠረት ላይ ማስቀመጥ አስፈላጊ መሆኑ፡፡
-
ለተማሪዎች አገልግሎት በጎ አስተዋጽኦ እያደረጉ ያሉ ቤተ-እምነቶችን ማመስገን፤ ለቀጣይም አገልግሎት ማበረታታት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ፡፡
በዝግጅቱ ላይ፣ ፕሮግራሙን በፀሎት የከፈቱት የኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነየሱስ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ቄስ ዶ/ር ኪሮስ ላቀው ነበሩ፡፡ ወንድም ሣሙኤል አሰፋ፤ በዝማሬ እንዲሁም ወንድም ዶ/ር ፍሬው ታምራት፣ ዘመኑን የሚዋጁ መሪዎች በሚል ርዕስ በኤፌሶን መጽሐፍ 5፡15-17 ላይ በመመስረት ቃለ እግዚአብሔርን ለታዳሚው በማቅረብ አገልግለዋል፡፡
ቀዳሚውን ጽሑፍ ያቀረቡት፣ ወንድም ጌቱ ግዛው ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች ታሪክ የተማሪዎች አገልግሎት ሚና በሚል ርዕስ አቅርበዋል፡፡ በጽሑፉ፣ የኢቫሱ ታሪካዊ አጀማመር የተዳሰሰ ሲሆን፣ የተማሪዎች አገልግሎት አስተዋጽኦ በኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች ዘንድ የሚለው ሐሳብ በጥልቀት ተዳሷል፡፡
ሁለተኛው ጽሑፍ የቀረበው በወንድም ሮቤል ጨመዳ፣ የኢቫሱ ዋና ጸሐፊ፣ ሲሆን የኢቫሱን ወቅታዊ ሁኔታ የሚያስዳስስ ነበር፡፡ በቀረበው ጽሑፍ፣ የኢቫሱ ወቅታዊ ሁኔታ፤ ድርጅታዊ አቋም፤ ዋና ዋና የአገልግሎት መስኮች፤ የተማሪዎች የዕለት ተዕለት መንፈሳዊ ተግባራት፤ ኢቫሱ በአዲስ ጎዳና፤ እና የአገልግሎቱ ተግዳሮቶች የሚሉት ነጥቦች በስፋት ተዳሰዋል፡፡
በመጨረሻው ጽሑፍ፣ የኢቫሱ-ቤተክርስቲያን የትብብር አቅጣጫዎች ማሣያ በሚል ርዕስ፣ በወንድም ማቲዎስ ትርሲተወልድ የቀረበው ነበር፡፡ የቀረበው ጽሑፍ፣ “ትብብር ለምን?” በሚል መጠይቅ በመነሳት፣ በትብብር መስራት ያለውን ጠቀሜታና ወቅታዊ አስገዳጅ ሁኔታዎች በስፋት የተመለከተ ነበር፡፡ በኢቫሱ አገልግሎት ዙሪያ በትብብር ሊያሰሩ የሚችሉ እድሎች፣ እንዲሁም በጋራ መስራትን የሚጠይቁ የጋራ ተግዳሮቶች ተጠቅሰዋል፡፡ በመቀጠልም፣ አብያተ ክርስቲያናት፣ ልጆቻቸው የሆኑ የካምፓስ ተማሪዎችን ለማገልገል በትብብር ሊሰሩባቸው የሚገቡ ፕሮግራሞችም ቀርበዋል፡፡ የቤተክርስቲያን ቤተሰብ ፕሮግራም (Family Program)፣ የካምፓስ ተማሪዎች ሕብረት አገልግሎት ንድፍ(Campus Students Fellowship) ፣ ስልጠና መስጠትና ልምድ ማካፈል፣ ተማሪ ተኮር ጥናትና ምርምር ማካሄድ፣ እንዲሁም የፋይናንስና ቁስ ሐብት ድጋፍ፣ አብያተክርስቲያናት ከኢቫሱ ጋር በትብብር ሊሰሩባቸው የሚችሉ አቅጣጫዎች መሆናቸው ተብራርቷል፡፡በስፋት ተዳሰዋል፡፡
በዝግጅቱ ከተካተቱት ፕሮግራሞች መካከል፣ ለቀድሞው የኢቫሱ ዋና ፀሐፊ፣ ወንድም ዘላለም አበበ የተደረገ ፀሎትና የዓለም አቀፉ የወንጌላውያን ተማሪዎች ሕብረት(IFES) ፕሬዝዳንት ያደረጉት ንግግር ይጠቀሳል፡፡ ወንድም ዘላለም አበበ፣ በዓለም አቀፉ የወንጌላውያን ተማሪዎች ሕብረት፣ የእንግሊዘኛና ፖርቹጋል ቋንቋ ተናጋሪ አፍሪካ ወንጌላውያን ተማሪዎች ሕብረቶችን(IFES-EPSA) እንዲያስተባባብር በፀሐፊነት መመረጡን ተከትሎ፣ በስራው ስኬታማ እንዲሆን፤ የእግዚአብሔርም እርዳታ ከእርሱ ጋር እንዲሆን ፀሎት ተደርጎለታል፡፡
የዓለም አቀፉ የወንጌላውያን ተማሪዎች ሕብረት (IFES) ፕሬዝዳንት፣ ዳንኤል ቦርዳኒ፣ ባደረጉት ንግግርም በእለቱ የተገኙትን የቤተክርስቲያን መሪዎችን አመስግነዋል፡፡ ምስጋናው የተበረከተው፣ ለተማሪዎች አገልግሎት እያበረከቱት ስላለው ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ እና ፣ ወንድም ዘላለም አበበን ለመሪነት የማብቃት ስራን በመስራት ለተሾመበት አገልግሎት ስለአበረከቱ ነበር፡፡ ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው፣ አብያተክርስቲያናት የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አገልግሎትን በፍጹም ችላ ማለት እንደሌለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ በተማሪዎች አገልግሎት ላይ በሌሎች ክፍላተ-ዓለማት እየተሰራ ያለውን አስደናቂ የእግዚአብሔር መንግስት ስራ እንደምሳሌ በማቅረብ፣ የቤተክርስቲያን መሪዎችና አጋር አካላት ከኢቫሱ አገልግሎት ጎን በመቆም አገልግሎቱን በቻሉት ሁሉ እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ኢቫሱ፣ እ.ኤ.አ. ከ1942 ጀምሮ የዓለም አቀፉ ወንጌላውያን ተማሪዎች ሕብረት አባል መሆኑ ይታወቃል፡፡
በዝግጅቱ የተካፈሉት ተሳታፊዎች፣ በቀረቡት ጽሑፎችና አጠቃላይ በኢቫሱ አገልግሎት ዙሪያ አስተያየቶችና ጥያቄዎችን በማንሳት ውይይት ተደርጓል፡፡ በውይይቱ ወቅት ተሣታፊዎች፣ ፕሮግራሙ ሰፊ ግንዛቤ እንዲጨብጡ እንደረዳቸው በመግለጽ፤ እንዲህ ዐይነት የግንዛቤ ማስጨበጫና የውይይት መድረክ በየዓመቱ መደረግ እንዳለበት አበክረው ተናግረዋል፡፡ ኢቫሱ፣ በጥቂት የሰው ኃይል የሚሰራቸው ትላልቅ ስራዎች እንዳስደነቃቸውም ተናግረዋል፡፡ ተሣታፊዎች እንደተናገሩት፣ ኢቫሱ ስራዎቹን በእንዲህ ዓይነት መልኩ ለቤተክርስቲያናት ካላቀረበ፣ አገልግሎቱን ለመደገፍም ሆነ የሚሰሩትን ስራዎች ለማወቅ አስቸጋሪ እንደኒሆን ተሳታፊዎች ገልጸዋል፡፡
በኢቫሱ-ቤተክርስቲያን ትብብር አቅጣጫዎች ዙሪያ በተነሱት ጉዳዮች ላይም በጋራ ለመስራት ሙሉ ፈቃደኝነቱ እንዳላቸው ሃሳባቸውን ያካፈሉ ተሳታፊዎች ተናግራዋል፡፡ ኢቫሱን በሚያስፈልገው ሁሉ ለማገዝ ፈቃደኛ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ለትብብር ቀና ናቸው ያሏቸውን የተለያዩ መንገዶችንም አያይዘው ጠቁመዋል፡፡ በፕሮግራሙ የተገኙት የልዩ ልዩ አብያተክርስቲያናት መሪዎች፣ ጉዳዩን በወከሉት ቤተእምነትና ተቋም በመውሰድ መደረግ ያለባቸውን ነገሮች እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡
በመጨረሻም፣ ፕሮግራሙን ሲመሩ የቆዩት የኢቫሱ የቦርድ ሰብሳቢ፣ ወንድም ፈቀደ ተፈራ፣ ተሣታፊዎችን ሁሉ ለተማሪዎች አገልግሎት እያበረከቱ ስላሉት ልዩ ልዩ ድጋፍ ምስጋና ካቀረቡ በኋላ ፕሮግራሙ በፀሎት ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡
ዝግጅቱ፣ የኢቫሱን አገልግሎ ለመደገፍ የልብ አንድነት የተንጸባረቀበት፣ ተሣታፊዎች ስለ ኢቫሱ አገልግሎት ጠቃሚ ግንዛቤ የጨበጡበትና በቀጣይ አብሮ ለማገልገል ትልቅ መነሳሳት የታየበት ሆኖ ተጠናቋል፡፡
እኛም፣ በዝግጅቱ የቀረቡትን ጽሑፎችን፣ ንግግሮችና ምስክርነቶች ለአንባቢ ጠቃሚ በሆነ መልኩ በጽሑፍና በምስልና በድምጽ በድህረ-ገጽ(www.evasue.net) እና ዩ-ቲዩብ (EvaSUE) በማዘጋጀት በቀጣይ አንድ በአንድ እንደምናቀርብ ከወዲሁ እናሳውቃለን፡፡