በኢትዮጵያ ወንጌላውያን ክርስቲያን ተማሪዎችና ምሩቃን ማሕበር (ኢቫሱ)፣ የሚዘጋጀው ዓመታዊው የዩኒቨርሲቲና ኮሌጅ ወንጌላውያን ክርስቲያን ተማሪዎች ሕብረቶች፣ የመሪዎች ጉባኤ ደብረዘይት በሚገኘው የመሠረተ ክርስቶስ ኮሌጅ ለስድስት ቀናት ሲካሄድ እንደነበረ የሚታወስ ሲሆን ቅዳሜ ማታ (ነሐሴ 13/2009 ዓ.ም) ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡
የጉባኤው መሪ ሐሳብ፣ በካምፓስ ውስጥ << ለኢየሱስ መኖር፤የኢየሱስ ምስክር መሆን>> የሚል ነበር፡፡ በስድስቱ ቀናቶች በዚሁ መሪ ሐሳብ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ትምህርቶችና ሴሚናሮች ተሰጥተዋል፡፡ በእግዚአብሔር የመቤዠት ታሪክ ውስጥ እግዚአብሔር ከሰዎች የሚፈልገው ዋና ነገር ምን እንደሆነ በጥልቀት ተዳሷል፡፡ የእግዚአብሔር የቀደመ አላማ (በፍጥረቱ መክበር) ፣ የሰው ልጅ ትልቁ ችግር (ኃጢአት)፣ የእግዚአብሔር ታላቅ ፍቅር (በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢአት ስርየትን መስጠት፤ የሰውን ልጅ ወደ መንግስቱ ዳግም በምህረት መመለስ)፣ ለሰዎች የተሰጠ ታላቁ ተልዕኮ (ኢየሱስ የጀመረውን ታላቁን ተልዕኮ ማስቀጠል)፣ ታላቁ ተስፋ (በክርስቶስ የዳኑት ሕዝቦች ከእግዚአብሔር ጋር በዘለአለም መንግስት ውስጥ መገኘት)፣ ከተዳሰሱት ሐሳቦች መካከል ይገኙበታል፡፡ የእግዚአብሔር የልቡ ሐሳብ የሰዎች በክርስቶስ አምኖ መዳን እንደሆነ ያስረገጠ ትምህርት ነበር፡፡
ትምህርቱ ቀጥሎ፣ የኢየሱስ ምስክር በመሆን ተግባር ውስጥ የመንፈስ ቅዱስ ሚና ምን እንደሆነ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን መሠረት በማድረግ ትምህርት ተሰጥቷል፡፡ እንደ አማኝ፣ ጥሪያችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር መሆን እንደሆነ፣ በዚህ ጥሪ ውስጥ የመንፈስ ቅዱስን ሚና፣ እንዲሁም የአማኞች ድርሻ ምን እንደሆነ ማሣየት የትምህርቱ ዋና ዋና ጭብጦች ነበሩ፡፡ <<ለኢየሱስ መኖርና የኢየሱስ ምስክር መሆን>>፣ በሚለው መሪ ሐሳብ ውስጥ የተዳሰሰው ሌላው ነጥብ አማኞች ከካምፓስ ውጪ በልዩ ልዩ ሥፍራ ኢየሱስን እያሣዩና ምስክር እየሆኑ መኖር እንደሚችሉ የቀረበ ትምህርት ነበር፡፡ በዝግጅቱ፣ አማኞች በተለይ በሥራ ቦታ የኢየሱስ ምስክር ለመሆን ማዳበር የሚገባቸውን ነገሮች ከተሞክሮ ጋር በማዋዛት በጥሩ ሁኔታ ቀርቧል፡፡
በከሰዓት ክፍለ ጊዜያት፣ የተማሪ መሪዎች ልዩ ልዩ ሴሚናሮችን እንዲካፈሉ ተደርጓል፡፡ መጽሐፍ ቅዱሣዊ መሪነት፣ የንዑስ ቡድን አገልግሎት፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚኖር ቁርኝት፣ ግቢዎችን በወንጌል መድረስ፣ ባለአደራነት፣ ሕብረት፣ ፀሎት፣ ደቀመዝሙር አድራጊ ንቅናቄ እና የኑፋቄ ትምህርቶችን የተመለከቱ አርዕስቶች በሴሚናሮቹ ከተዳሰሱት መካከል ይገኙበታል፡፡ ሌላው በጉባኤው ከተከናወኑት ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል፣ የኢቫሱን ‘ስትራቴጂክ ፕላን’ አስመልክቶ የተደረገው የቡድን ውይይት ተጠቃሽ ነው፡፡ የተማሪ መሪዎቹ፣ የኢቫሱን ጠንካራ ጎን፤ ክፍተት መስሎ የታያቸውን፤ እንዲሁም በቀጣይ ዓመታት በአገልግሎቱ ትኩረት ውስጥ ቢካተቱ ያሏቸውን ሀሳቦች አንስተው ተወያይተዋል፡፡
በጉባኤው፣ ከዚህ ቀደም እንደሚደረገው፣ ከተማሪ መሪዎች ጋር የካምፓስ ሕብረቶች አገልግሎትን አስመልክቶ ውይይት ተካሂዷል፡፡ መድረኩን የመሩት የተማሪ ካውንስል መሪዎች ሲሆኑ፣ በውይይት ወቅት ብዙ አጀንዳዎች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ የካምፓስ አገልጋዮች ይመደቡልን፣ የስህተት አስተምህሮዎችን በተመለከቱ መደረግ ስለሚገባቸው ነገሮች፣ ከቦታና ከአንዳንድ አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ አካሄዶች ምን መምሰል እንዳለባቸው ውይይት ከተደረገ በኋላ ከኢቫሱ በኩል ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ጉባኤው ከመፈታቱ ከአንድ ቀን በፊት በነበረው ስብሰባ፣ ሀገር አቀፍ የካምፓስ ወንጌላውያን ክርስቲያን ተማሪዎች ሕብረቶች የጋራ የፀሎት ጊዜያቶችን ወስነዋል፡፡ የመጀመሪያው የፀሎት ጊዜ ከጥቅምት 20 – 25/ 2010 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን፤ ሁለተኛው የፀሎት ጊዜ ከ መጋቢት 3 – 8 /2010 ዓ.ም የሚካሄድ ይሆናል፡፡ በተጠቀሱት የፀሎት ጊዜያቶች የመጨረሻዎቹ ቀናቶች በሁሉም ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ወንጌላውያን ክርስቲያን ተማሪዎች ሕብረቶች በተመሣሣይ ጊዜያቶች የሚከናወኑ ሲሆኑ፣ በተቀሩት ቀናቶች ግን እንደየግቢዎች ተጨባጭ ሁኔታ የሚካሄዱ ይሆናል፡፡ በፀሎት ጊዜያቶቹ ከሚነሱት አርእስቶች መካከል፣ የግል ህይወት ተሃድሶ፣ ስለ ቤተክርስቲያን፣ መንፈስ ቅዱስን በመጠማት እንዲሁም ሰለ ሀገር እንዲጸለይ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
የ2009 ዓ.ም የተማሪ መሪዎች ጉባኤ በብዙ መልኩ ከዚህ በፊት ከተደረጉት ሁሉ የተለየ መሆኑ አንዱ ክስተት ነበር፡፡ ጉባኤው ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ ውጪ መካሄዱ፣ የተሣታፊ መሪዎች ቁጥር ከዚህ በፊት ከነበረው ቁጥር በሶስት እጥፍ መጨመሩ፣ የፕሮግራም ይዘቱ ለፀሎት ከፍተኛውን ቦታ መስጠቱና የተማሪ መሪዎችም በጉባኤው ለተካሄዱት ፕሮግራሞች የሰጡት ከፍተኛ ትኩረትና የነበራቸው መልካም ተሣትፎ የጉባኤው ዐይነተኛ መገለጫዎች ነበሩ፡፡
የዚህ ዓመት ጉባኤ የተማሪ መሪዎችን በብዙ መልኩ ያስታጠቀ፣ ለተግባራዊ አገልግሎትም እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦች የተነሱበት ሆኖ ለ ስድስት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ ቆይቶ ትላንት እሑድ (ነሐሴ 14/2009 ዓ.ም) ተጠናቋል፡፡ ተሣታፊ የተማሪ መሪዎችም ለ 2010 ዓ.ም አገልግሎት ስንቅን ሰንቀው ወደመጡበት ተመልሰዋል፡፡ እኛም፣ በጉባኤው የተሰጡትን ትምህርቶች፣ ሴሚናሮችና አስደናቂ መስክርነቶች በፎቶና በቪዲዮ፣ እንዲሁም በጽሑፍ አዘጋጅተን በማህበራዊ ድኅረገጽና ዌብሣይት እንዲሁም በዩቲዮብ አድራሻችን እንደምናቀርብ ቃል እንገባለን፡፡
በመጨረሻም፣ በጉባኤው ላይ በማስተማር ለተሣተፉት፣ ፕሮግራሞቹን በማስተባበርና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ በአንድም በሌላም መልኩ ድርሻ ለነበራቸው ሁሉ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ተማሪዎችና ምሩቃን ማኅበር (ኢቫሱ)፣ ልባዊ ምሥጋናውን ያቀርባል፡፡
ግሩም ጊዜ ነበር፡፡ ወጣቶች በአንድነት ወደ አንድ ግብ ሲዘምቱ ከማየት በላይ ምን የሚያስደስት ነገር አለ? … ቤተክርስቲያን ሆይ ተተኪ ትውልድሽ ይኸው!