Call: +25111249226 • +251118333094

E-mail: info@evasue.net

የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን ተማሪዎችና ምሩቃን ማህበር (ኢቫሱ)
Evangelical Students’ and Graduates’ Union of Ethiopia

የ2010 ዓ.ም የክርስቶስ ልዕልና ጉባኤ

በኢቫሱ የመካከለኛው ክልል ቢሮ በየዓመቱ የሚካሔደው የኢየሱስ ክርስቶስ ልዕልና ትምህርታዊ ጉባኤ፣ በተማሪዎች አልፎም በአዲስ አበባ እና አካባቢው ባሉ ምሩቃን፣ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እና የቤተክርስቲያን ወጣቶች ዘንድ ተጠባቂ እየሆነ የመጣ ፕሮግራም ነው፡፡ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ የተደረገው የኢየሱስ ክርስቶስ ልዕልና ኮንፍራንስ በምስራቅ መሰረተ ክርስቶስ ቤተክርሰቲያን፣ ከየካቲት 23 እስከ 25 2010 ዓ.ም ድረስ፣ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ተካሂዷል፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ በ2007 ዓ.ም በቤዛ ዓለም አቀፍ ቤተ-ክርስቲያን የማምለኪያ አዳራሽ በተካሄደ ጊዜ፣ ከአንድ ሺ (1,000) በላይ ተማሪዎች ተገኝተው ነበር፡፡ በወቅቱ የቆላስያስ መፅሐፍ ሐተታ የተደረገ ሲሆን፤ ጉባዔውም የክርስቶስ ልዕልና (Supremacy of Christ) የሚለውን ስያሜ ያገኘው በዚሁ የመጀመርያ ጉባኤ ላይ ነው፡፡ “… እርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ …” ከሚለው የቆላስያስ 1፡18 ክፍል ላይ በመውሰድ ክርስቶስ በሁሉም ነገር ላይ ልዕልና እንዳለው ለማስገንዘብ የክርስቶስ ልዕልና ጉባኤ ተባለ፡፡

Supremacy-of-Christ-2

ሁለተኛው የክርስቶስ ልዕልና ጉባኤ በምስራቅ መሰረተ ክርስቶስ ቤተ-ክርስቲያን የማምለኪያ አዳራሽ፣ በ2008 ዓ.ም በወርሃ የካቲት፣ ክርስቶስ ከሁሉ በላይ ነው በሚል መሪ ቃል ሲካሔድ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ ተማሪዎች ታድመውበት ነበር፡፡ ቀጥሎም በ1ኛ ቆሮንቶስ ላይ ተመርኩዞ “እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካልን” በሚል መሪ ሀሳብ በ2009 ዓ.ም ወርሃ መጋቢት ከሁለት ሺ (2,000) በላይ ተማሪዎች በተገኙበት በምስራቅ መሰረተ ክርስቶስ ቤተ-ክርስቲያን የማምለኪያ አዳራሽ መካሔዱ የሚታወስ ነው፡፡ ዘንድሮም በዚያው በምስራቅ መሰረተ ክርስቶስ ቤተ-ክርስቲያን የማምለኪያ አዳራሽ፣ ለአራተኛ ጊዜ ከሁለት ሺ( 2,158) አንድ መቶ ሃምሳ ስምንት በላይ ተማሪዎች እና ከአራት መቶ (400) በላይ የመሰናዶና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ ምሩቃን እና ከተለያየ ቤተ-ክርስቲያናት የመጡ የወጣት አገልጋዮች በተገኙበት ተካሒዷል፡፡ በዚህ ዓመት የተካሔደው ጉባኤ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ልዕልና በሮሜ መልዕክት ውስጥ በሚል ሲሆን፤ “በወንጌል አላፍርምና . . .”፣ የሚለው የሮሜ 1፡16 መልዕክት የጉባኤው መሪ ቃል ነበር፡፡ ጉባኤው ዓርብ ጠዋት ጀምሮ ዕሁድ ከሰዓት የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ከዕሁድ ጠዋት ውጪ፣ መርሐ ግብሩ፣ በሶስት ቀን በአምስት ክፍለ-ጊዜዎች ተከፋፍሎ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ አምልኮ፣ የሮሜ መፅሐፍ የእያንዳንዱ ምዕራፍ የቃል ንባብ፣ የክርስቶስ ልዕልና በሮሜ መልዕክት ትምህርት እና ዓውደ-ርዕይ በመርሀ ግብሩ ውስጥ የተካተቱ ዐበይት ድርጊቶች ነበሩ፡፡

በመጀመርያው ክፍለ ጊዜ፣ መጋቢ ተሾመ ዳምጠው ከሮሜ 1፡1-2 በመነሳት የሮሜ መልዕክት ማዕከላዊ ሀሳብ የእግዚአብሔር ወንጌል እንደሆነ፤ የወንጌሉም ማዕከል ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ በትምህርታቸው መግቢያ ላይ አብራርተው፣ በዚሁ መነሻነት በጠቅላላው የሮሜ መልዕክት ውስጥ የኢየሱስን ማንነት አሳይተዋል፡፡ በሁለተኛው ክፍል ጊዜ ወንድም አብርሃም ተክለማርያም የሮሜ መልዕክትን አውድና ታሪካዊ ዳራ ትንታኔ አቅርበዋል፡፡ የመጽሐፉን አከፋፈል፣ የፀሐፊውን አላማ፣ ፀሐፊውና የመልዕክቱ ተቀባዮች የነበራቸውን ግንኙነትም በጥልቀት አሳይተዋል፡፡ ወንድም አብርሃም በትምህርታቸው መደምደሚያ ላይ መልዕክቱን በሁለት ትልልቅ ክፍሎች ሊከፈል የሚችል እንደሆነ ሲያስረዱ፤ የመጀመርያዎቹ አስራ አንድ ምዕራፎች በአመዛኙ መሠረታዊ የክርስትና አስተምህሮ እና ቀጣይ አራት ምዕራፎች ደግሞ ተግባራዊ የክርስቲያን ህይወት ምን መምሰል እንዳለበት እንደሚናገር አስገንዝበዋል፡፡ አያይዘውም፣ ለታዳሚዎቹ እንዲህ ብለዋል፣ “አሁን እንደ ተማሪ በካምፓስ ነው ያላችሁት ጨርሳችሁ ስትሄዱ አንድ አጥቢያ ቤተ-ክርስቲያን መቀላቀል እና አባል መሆን ይገባችኋል፡፡ የሮሜ መልዕክት ከምዕራፍ አስራ ሁለት በኋላ ያለውን ተግባራዊ የክርስቲያን ህይወት መለማመድ የሚቻለው በአማኞች መካከል ነው፡፡ በስራ ወደ ሌላ ከተማ፣ ከሀገር ውጪ ብትወጡ በማንኛውም ቦታ ብትሆኑ ከአማኞች መካከል መደባለቅ አለባችሁ፤ ለዛውም በአማኞች መካከል ንቁ አካል በመሆን ነው ልትደባለቁ የሚገባው” ሲሉ ትምህርታቸውን ደምድመዋል፡፡

በሁለተኛው ቀን የመጀመርያ ክፍለ-ጊዜ ዶ/ር ማሙሻ ፈንታ በመግቢያቸው ላይ የሮሜ መፅሐፍ አስደናቂነትን እንዲህ በማለት በመግለፅ ነበር ትምህርቱን የጀመሩት “ሮሜ አስደናቂ ወንጌል ነው . . . ወንጌል ተጠቅጥቆ አንድ ላይ ሆኖ ተጠቃሎ የሚገኝበት መፅሐፍ ነው፡፡ ምን አልባትም ደግሞ የአብዛኞቻችን መዳን ወደ ክርስቶስ መምጣት ወደ ኋላ ሊፈተሽ ቢሞከር የሮሜ መፅሐፍ ሚና የላቀ ነው፤ ሲመሰከርልን ከሰማናቸው ጥቅሶች አብዛኞቹ ከሮሜ መፅሐፍ የወጡ ናቸው . . .፡፡ ሮሜ ግልፅ አድርጎ ስለ ሰው ኃጢአተኝነት፣ ስለ ክርስቶስ አዳኝነት እና የእምነት አስፈላጊነት የሚናገር መፅሐፍ ነው፡፡ ይህ በእኛ የማመን ታሪክ ብቻ ሳይሆን በብዙ ትልልቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ታሪክ ውስጥም ተንፀባርቋል፡፡ ከቅዱስ አውገስጢኖስ ጀምሮ . . . እስከ በአውሮፓ የተቀጣጠለው ተሀድሶ ዋና ሞተር ማርቲን ሉተር ድረስ በጣም ብዙዎቹን የእምነት አባቶች ወደ ጌታ ያመጣቸው የሮሜ መፅሐፍ ነው፡፡” የሮሜን መልዕክት ሙሉ ለሙሉ ለመተንተን በሶስት ቀን የማይቻል መሆኑን የገለፁት ዶ/ር ማሙሻ በወፍ በረር ዋና ዋና ክፍሎች ላይ ጊዜ በመውሰድ ሰብከዋል፡፡ በዚሁም መሰረት የሮሜን መልዕክት ፍሰት መሰረት በማድረግ ለማስተማር እና ለታዳሚው የወደፊት የግልና የቡድን ጥናት እንዲመች በሰባት ክፍሎች በመክፈል ለሁለት ቀን በሶስት ክፍለ ጊዜ አስተምረዋል፡፡

Dr.-Mamusha

† የመጀመርያው ከሮሜ 1፡1 እስከ 1፡17 ድረስ፡- የሮሜ መልዕክት መግቢያ፣
† ሁለተኛው ከሮሜ 1፡17 እስከ 3፡20 ድረስ፡- የእግዚአብሔ ፅድቅ በቁጣ እና በፍርድ ሲገለጥ፣
† ሶስተኛው ከሮሜ 3፡21 እስከ 4፡25 ድረስ፡- የእግዚአብሔር ፅድቅ በክርስቶስ ኢየሱስ በማዳን ሲገለጥ፣
† አራተኛው ከሮሜ 5፡1 እስከ 8፡39 ድረስ፡- የእግዚአብሔር ፅድቅ በቅድስና ፍሬ ሲገለጥ፣
† አምስተኛ ከሮሜ 9፡1 እስከ 11፡36 ድረስ፡- የእግዚአብሔር ፅድቅ በአሁን የእስራኤል ሁኔታና በወደፊት ተስፋዋ ሲገለጥ፣
† ስድስተኛው ከሮሜ 12፡1 እስከ 15፡33 ድረስ፡- የእግዚአብሔር ፅድቅ በተግባራዊ ህይወት ሲገለጥ እና
† የመጨረሻው ሮሜ ምዕራፍ 16፡- ስንብት እና ሠላምታ ናቸው፡፡

“ሮሜ አስደናቂ ወንጌል ነው . . . ወንጌል ተጠቅጥቆ አንድ ላይ ሆኖ ተጠቃሎ የሚገኝበት መፅሐፍ ነው፡፡ ምን አልባትም ደግሞ የአብዛኞቻችን መዳን ወደ ክርስቶስ መምጣት ወደ ኋላ ሊፈተሽ ቢሞከር የሮሜ መፅሐፍ ሚና የላቀ ነው፤ ሲመሰከርልን ከሰማናቸው ጥቅሶች አብዛኞቹ ከሮሜ መፅሐፍ የወጡ ናቸው . . .፡፡ ሮሜ ግልፅ አድርጎ ስለ ሰው ኃጢአተኝነት፣ ስለ ክርስቶስ አዳኝነት እና የእምነት አስፈላጊነት የሚናገር መፅሐፍ ነው፡፡ ይህ በእኛ የማመን ታሪክ ብቻ ሳይሆን በብዙ ትልልቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ታሪክ ውስጥም ተንፀባርቋል፡፡ ከቅዱስ አውገስጢኖስ ጀምሮ . . . እስከ በአውሮፓ የተቀጣጠለው ተሀድሶ ዋና ሞተር ማርቲን ሉተር ድረስ በጣም ብዙዎቹን የእምነት አባቶች ወደ ጌታ ያመጣቸው የሮሜ መፅሐፍ ነው፡፡”

በጉባኤው ላይ የተማሪ ህብረቶች የህብረ ዝማሬ ቡድኖች ጥዑም ለዛ ያላቸው የኢየሱስን ልዕልና የሚያውጁ መዝሙሮችን አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም እሑድ ከሰዓት በኋላ የተወደደ ወንድም ዘማሪ አቤንኤዘር ለገሰ ከየህብረቶቹ ከተውጣጡ የተማሪ የህብረ ዝማሬ ቡድን ጋር በመሆን በዝማሬ ጉባኤውን መርቷል፡፡ አቤንኤዘር በእለቱ የ2001 ዓ.ም የአምቦ ምሩቅ እና የኢቫሱ በጎ ፈቃደኛ አገልጋይ እንደነበር አስታውሶ በኢቫሱ የተማሪዎች ህብረት የሚሰጡ እንዲህ አይነት ትምህርቶች እንዴት በህይወቱ ላይ በጎ ተፅዕኖ አንዳሳረፉ ሲናገር፣ “የህይወት አቅጣጫዬን ከለወጡ ነገሮች መካከል ዋነኛውን ስፍራ የሚወስደው በኢቫሱ የነበረኝ የአገልግሎት ቆይታ ነው፡፡ ወደ ፊት ምን አይነት ሰው መሆን እንዳለብኝ፤ በምን አይነት መንገድ ላይ መገኘት እንዳለብኝ አቅጣጫዎቼን የቀየሩት እንደዚህ አይነት በኢቫሱ የተማሪዎች ህብረት የሚዘጋጁ ጉባኤዎች ናቸው፣” ካለ በኋላ “በዚያን ጊዜ ያከማቸኋቸው ብዙ የትምህርት ክምችቶች ናቸው አሁን እየመነዘርኩ ለህይወቴ እና አገልግሎቴ የምጠቀመው፡፡ ነገር ግን በዚያን ጊዜ አይመስለኝም ነበር አሁንም እናንተ ላይመስላቸሁ ይችላል ግን በርግጠኝነት የምነግራችሁ እንደማትጎዱ ነው” ብሏል፡፡ በተጨማሪም በጉባኤው ላይ ከአስራ ስድስት ግቢዎች የተውጣጡ ተማሪዎች አስራ ስድስቱን የሮሜ ምዕራፎች በቃላቸው አጥንተው አቅርበዋል፡፡

ለመጀመርያ ጊዜ ዘንድሮ ከቋሚ መርሀ ግብሩ ጎን ለጎን ዐውደ ራዕይ ተካሒዷል፡፡ በአውደ ራዕዩ ላይ ሀያ ሁለት የሚሆኑ የተለያዩ የካምፓስ ህብረቶች፣ የመጸሐፍ ቅዱስ ኮሌጆች እና መንፈሳዊ ስራ የሚሰሩ አገልግሎቶች የተሳተፉ ሲሆን፤ በዚህ አውደ ራዕይ ላይ ተማሪዎች መንፈሳዊ ስራ ከሚሰሩ አገልግሎቶች እና የመጸሐፍ ቅዱስ ኮሌጆች ጋር ተዋውቀዋል፡፡ የካምፓስ ህብረቶች ደግሞ ስራዎቻቸውን ለተቀረው ማህበረሰብ አስተዋውቀዋል፡፡ በተጨማሪም በካምፓስ ህብረቶች መካከል የእርስ በእርስ ልምድ ልውውጥ እና ትስስር እንዲያደርጉ እረድቷል፡፡
በጉባኤው ላይ የኢቫሱ የስራ አስኪያጅ ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ፈቀደ ተፈራ ባደረጉት ንግግር በጉባኤው በጣም ደስተኛ እንደሆኑ ከተናገሩ በኃላ ከኢያሱ መጽሐፍ ምዕራፍ አንድ ቁጥር አምስት በመነሳት “ኢያሱ ቀጣዩ ምንድነው እያለ በተጨነቀበት ጊዜ እንደ ምሳሌ የሚሆነው ሰው ከአጠገቡ በተወሰደበት ወቅት እግዚአብሔር ድምፅ ነበረው፡፡” ያሉት አቶ ፈቀደ “በዚህም ዘመን እግዚአብሔር ከእናንተም ጋር ለቤተ ክርስቲያን ደግሞም ለሀገራችን ጉዳይ አለው በተለየ መንገድ ሊናገራችሁ የፈለገበት ወቅት ነው::” ካሉ በኃላ “እግዚአብሔር መልዕክት አለው የምትሔዱበትን አቅጣጫ ሊያሳያችሁ ፈልጓል የኢያሱን ህይወት የለወጠ ድምፅ የእናንተንም ህይወት የሚለውጥ ድምፅ ነው፡፡ ስለዚህ በንቃት እግዚአብሔርን ስሙት በአላማ ከእናንተ ጋር ለመነጋገር ይፈልጋል ስለዚህ አድምጡት” ሲሉ ምክር አስተላልፈዋል፡፡ በተጨማሪም አቶ ፈቀደ የተለያዩ ለዚህ ጉባኤ መሳካት አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል፡፡

የጉባኤውን አስፈላጊነት አስመልክቶ የኢቫሱ መካከለኛው ክልል አስተባባሪ የሆኑት ያዕቆብ ማሜ ሲናገሩ “የክልላዊ ቢሮዎች ዋነኛ ሃላፊነት የወንጌላውያን ክርስቲያን ተማሪዎች በካምፓስ የኢየሱስ ክርስቶስ ህያው ምስክሮች እንዲሆኑ፤ ህይወታቸውን በእውነተኛ አስተምህሮ እና ተግባር ላይ እንዲመሰረት ማስታጠቅ ነው፡፡ የክርስቶስ ልዕልና ጉባኤ ደግሞ ይህን ለማድረግ የምንጠቀምበት አንዱ መሣርያ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የኢቫሱ መካከለኛው ክልል በተማሪ ቁጥር እና በሚሸፍነው ቦታ ከስምንቱ የኢቫሱ ክልሎች ትልቁ ነው ሲሆን፤ በስሩ ሃያ አራት የመንግስት እና አርባ ሰባት የግል የካምፓስ ወንጌላውያን ክርስቲያን ተማሪዎች ህብረቶችን አቅፎ ይዟል፡፡

በጉባዔው ማጠናቀቅያ ላይ ተማሪዎች ስለ ፕሮግራሙ፣ እየተደነቁ እና እግዚአብሔርን እያመሰገኑ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ እግዚአብሔር እንዴት እንደተናገራቸውም ገልፀዋል፡፡ ከነዚህም መካከል የዩኒቲ የኒቨርሲቲ ሶስተኛ አመት የአርክቴክቸር እና አርባን ፕላኒንግ ተማሪ የሆነው ሳሙኤል፣ “ኢየሱስ በህይወቴ ትልቅ ቦታ እንዳለው በትልቁ የተረዳሁበት ጉባኤ ነው፡፡ ስለሆነም በትምህርቴ፣ በቀን ለቀን ምልልሴ እና አገልግሎቴ ሁሉ ኢየሱስ የበላይ እንደሆነ እና እርሱን አልቄ ማሳየት እንዳለብኝ ተረድቻለሁ” ብሏል፡፡ በተጨማሪም የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ አምስተኛ ዓመት የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ የሆነው ቃልኪዳን ደምሰው፣ በዚህ ዓመት ለሶስተኛ ጊዜ እንደተገኘ ገልፆ “በሶስቱም ጊዜ የክርስቶስ ልዕልና ጉባኤ ላይ ስገኝ ያገኘሁት ነገር መጸሐፍት ሁሉ ስለኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚናገሩ፤ እርሱን ብቻ የሚያልቁ እንደሆኑ ተረድቻለሁ” ብሏል፡፡

Fekede-Tefera

ከባለፈው 2009 ዓ.ም ጀምሮ የመካከለኛው ኢቫሱ ክልል ካዘጋጃቸው ጉባኤዎች ልምድ በመነሳት ጉባኤው በኢቫሱ ምስራቅ ክልል ድሬዳዋ መካሔድ የጀመረ ሲሆን ዘንድሮ በክልሉ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሚካሔድ ይጠበቃል፡፡ በተጨማሪም በሰሜን ምዕራብ የኢቫሱ ክልል ባህር ዳር ከተማ እና በደቡብ ኢቫሱ ክልል ሀዋሳ ከተማ ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ ጉባኤው በተመሳሳይ ሁኔታ ተካሂዷል፡፡

Latest Articles

Latest video