የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ወንጌላውያን ክርስቲያን ተማሪዎች ህብረት
አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ወንጌላውያን ክርስቲያን ተማሪዎች ሕብረት፣ የተመሰረተበትን 30ኛ ዓመት አክብሯል፡፡ ዝግጅቱ የተካሄደው ከሚያዝያ 26 – 28/2010 ዓ.ም፣ ለሦስት ቀናት ነበር፡፡የፕሮግራሙ ዋና አላማ፣ የህብረቱን 30ኛ የምስረታ ዓመት ተንተርሶ፣ እግዚብሔርን ማመስገንና ማምለክ፤ ምሩቃንንና ተማሪዎችን በማቀራረብ አብረው እንዲሰሩ ማነሳሳትና ህብረቱን እስከ አሁን እየደገፉ ያሉትን ምሩቃንና ሌሎች አካላትን ማመስገን ነበር፡፡ ፕሮግራሙ፣ ሚያዝያ 26/2010 ዓ.ም ዕለተ አርብ ምሽት ከ12፡00-3፡30 በአርባምንጭ ኤሊም ሎጅ ፣ከተለያዩ ቦታዎች ለመጡ ምሩቃን የእንኳን ደህና መጣችሁ እና የእራት ግብዣ በማድረግ ተጀምሯል፡፡
የዝግጅቱ ተሣታፊ እንዲሆኑ ከቀድሞ ምሩቃን በተጨማሪ፣ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም ተገኝተዋል፡፡ ከእነዚህም መሀከል፣ ከህብረቱ ጋር ሲሰሩ የቆዩ የአጥቢያ ቤተክርስቲያን መሪዎች( የመካነ ኢየሱስ፣ የሙሉ ወንጌልና የቃለ ህይወት)፣ የጋሞ ጎፋ ዞን እና አካባቢው አብያተክርስቲያናት መሪዎች፣ የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት፣ የዋናው ግቢ የወንጌላውያን ክርስቲያን ተማሪዎች ህብረት ሲመሰረት አካባቢ የነበሩና ትልቅ ዋጋ የከፈሉ አባት፣ ዶክተር መርጊያ ባልቻ እና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኙበታል፡፡
ፕሮግራሙ የተጀመረው በፀሎት ሲሆን፣ ከተገኙት እንግዶች መካከል ዶክተር መርጊያ ባልቻ፣የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ራሔል ኤልያስ፣ የጋሞ ጋፋ ዞን አብያተክርስቲያናት ሰብሳቢ አቶ ቦሻ ቦምቤ፣ የኢቫሱ የካምፓስ አገልጋይ ወንዱ ሱማሌ እና የህብረቱ ዋና ሰብሳቢ ወንድም ኦልቻ ጋዲሳ የመክፈቻ ንግግርና የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በዕለቱም፣ በኢቫሱ የካምፓስ አገልጋይ፣ ወንዱ ሱማሌ፣ አማካይነት ስለ ኢትዮጵያ ወንጌላዊያን ተማሪዎችና ምሩቃን ማህበር(ኢቫሱ) የቀደሙ ስራዎች፣ አሁን እየተሰሩ ስላሉት እና ወደፊት ሊሰሩ በእቅድ ስለተያዙት ስራዎች አጭር ገለፃ ተሰቷል፡፡ በተጨማሪም፣ ስለ ዋናው ግቢ ህብረት እንቅስቃሴዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለፃ ተደርጓል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ፣ ከህብረቱ ጋር በትጋት ሲሰሩ ለነበሩ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡ የዕለተ–ዐርብ መርሐ ግብር፣ እራት ከተበላ በኋላ፣ በዝማሬና በፀሎት ተዘግቷል፡፡ ሚያዝያ 27/2010 ዕለተ–ቅዳሜ ከጠዋት 2፡30-6፡00 ሰዓት ከሁሉም የህብረቱ አባላት ጋር በልማት ዩኒቨርሲቲ ዳር ቃለህይወት ቤተክርስቲያን፣ የአምልኮና የቃል ጊዜ እንዲሁም የፀሎተ ጊዜ ነበር፡፡ በዕለቱ የእግዚአብሔርን ቃል ለህዝበ ምዕመናኑ በማካፈል ያገለገለው፣ የ1990ዎቹ ምሩቅ የነበረው ወንድም ዮፍታሔ ዮሐንስ ሲሆን፣ ስለእግዚአብሔር መንግስት ተፅዕኖ አገልግሏል፡፡ እግዚአብሔር መልካምነቱን ያሳየበት የተባረከ ጊዜም ነበር፡፡ በዚሁ ቀን ከሰዓት ከ8፡30 ጀምሮ እስከ 11፡00 ምሩቃን፣ ቀድሞ ሲያገለግሉባቸው የነበሩትን የአገልግሎት ዘርፎች በመጎብኘት ከእነርሱም ጋር ልዩ የአንድነት ጊዜ በሴሊሆም (የህብረቱ ማምለኪያ ቦታ) ላይ አሳልፈዋል፡፡ በፀሎት ተዘግቷል፡፡ በዕለቱ፣ ምሽት ላይ ከ12፡00 ጀምሮ በልማት ዩንቨርሲቲ ዳር ቃለ ህይወት ቤተክርስቲያን፣ የአምልኮ እና የቃል ጊዜ ነበር፡፡ በቃል ያገለገለው የቀድሞ የ80ዎቹ ዓ.ም የህብረቱ ምሩቅ የነበረው ነቢይ ሄኖክ ተሾመ ነበር፡፡
ሚያዝያ 28/2010 ዓ.ም፣ ዕለተ እሑድ፣ ምሩቃንና የህብረቱ አባላት የሆኑ ተማሪዎች፣ ወደ ጫሞ መዝናኛዎች ሄደዋል፡፡ በዚያም ጥሩ የአንድነትና የትውውቅ ጊዜ አሳልፈዋል፡፡ በመጨረሻም፣ በምሽት መርሐ ግብር፣ በአርባ ምንጭ እናት ሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን፣ የአምልኮ የቃል፣ እና የፀሎተ ጊዜ ተካሂዷል፡፡ በዕለቱ በቃል ያገለገለው፣ ነቢይ ሄኖክ ተሾመ፣ ነገርን በጊዜው በሚል ሀሳብ የእግዚአብሔርን ጊዜ ስለመጠበቅ አስተምሯል፡፡ ለተማሪዎችም ፀሎት ተደርጓል፡፡ እጅግ የተባረከ ጊዜም ነበር፡፡ በዕለቱ ዶክተር መርጊያን ጨምሮ ይህንን ፕሮግራም በማስተባበር ላገለገሉት ተማሪዎችና ለኢቫሱ የካምፓስ አገልጋዮች ስጦታ ተበርክቷል፡፡ የህብረቱ የ30ኛ ዓመት በተመለከተ፣ አጭር ታሪክ ተነቧል፡፡
ሦስት ቀን የፈጀው በዓል፣ የኬክ ቆረሳ በማድረግ፣ በዝማሬ-አምልኮ እና በፀሎት ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ ፕሮግራሙ በተካሄደባቸው ቀናቶች ሁሉ የእግዚአብሔር ታላቅ መገኘት በጉባኤው ላይ እንደነበር የብዙ ተሣታፊዎች ምስክርነት ነበር ፡፡ የእግዚአብሔር አብሮነት በኃይል ስለነበረ እጅግ አስደናቂ የሆነ የፀሎት ሪቫይቫል በፕሮግራሙ ላይ ተስተውሏል፡፡ ስለ ሀገራችን ኢትዮጵያም ጥብቅ ፀሎት ተደርጓል፡፡
ክብር ሁሉ ለታረደው በግ ለኢየሱስ ይሁን!!
በ ወንዱ ሱማሌ፣ ደቡብ ኢቫሱ ቢሮ