“. . . አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤ በታላቅም ድምፅ እየጮሁ። በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው አሉ።” ራእይ 7:9
በታኅሳስ ወር በሀገር አቀፍ ደረጃ በሀያ ሁለት ካምፓሶች ውስጥ ዘጠና ሁለት ተማሪዎች ጌታን ተቀብለዋል፡፡ እነዚህ ወንድሞች እና እህቶች በዋናነት ወደ ጌታ የመጡት በተማሪዎችና በክርስቲያን የተማሪ ህብረቶች ውስጥ በሚካሔድ የንዑስ ቡድኖች እና በመደበኛ የህብረቱ አገልግሎት አማካኝነት ነው፡፡
በጥቅምት እና ኅዳር በካምፓሶች ከሀገራዊ ያለመረጋጋቱ ጋር በተያያዘ በአብዛኞቹ ካምፓሶች በተደጋጋሚ ተማሪዎች ከግቢ ሲወጡና ሲመለሱ መቆየታቸውን የሚታወስ ሲሆን፤ በታኅሳስ ወር በአመዛኙ በካምፓሶች አካባቢ የነበረው አለመረጋጋት ቀንሶአል፡፡ በጥቅምት እና ህዳር ወር ብቻ በድምሩ ሁለት መቶ ስልሳ ተማሪዎች ወደ ጌታ መምጣታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ በዚህ ቁጥር ላይ በታህሳስ ወር የዳኑት ዘጠና ሁለት ተማሪዎች ሲደመሩ በነዚህ ሶስት ወራት የዳኑትን ተማሪዎች ቁጥር ወደ ሶስት መቶ ሀምሳ ሁለት ከፍ ያደርገዋል፡፡
ኢቫሱ ተማሪዎችን በደቀመዝሙር ሕይወት ለማሣደግና ለመባዛት፣ እንደ ዋና ስልት አድርጎ እየተገበረ ያለው አሠራር የንዑስ ቡድን አገልግሎት ጽንሰ ሀሳብን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ተማሪዎች በቡድናቸው ሲገኛኙ ከሚጠያየቁት የማደጊያ ግቦች አንዱና ዋናው የምስራቹን በዙሪያቸው ላሉ ሌሎች ሰዎች የማድረስ ሐላፊነታቸውን እየተወጡ እንደሆነ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ የእግዚአብሔርን ቃል ለመታዘዝ ያጠናሉ፤ አብረው ያመልካሉ፤ ይፀልያሉ እንዲሁም ህብረተሰብ ይፈጥራሉ፡፡ በዚሁ መሰረት ነው ባለፉት ሶስት ወራት ሶስት መቶ ሀምሳ ሁለት ተማሪዎች ወደ ጌታ የመጡት፡፡