“መከሩስ ብዙ ነው፥ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዴህ የመከሩን ጌታ ለመከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት።”
ሉቃስ 10፡2
በጥቅምት ወር በሀገር አቀፍ ደረጃ በአስራ አምስት ካምፓሶች ውስጥ አርባ አንድ ሰዎች ጌታን ተቀብለዋል፡፡ እነዚህ ወንድሞች እና እህቶች በዋናነት ወደ ጌታ የመጡት በተማሪዎችና በክርስቲያን የተማሪ ህብረቶች ውስጥ በሚካሔድ የንዑስ ቡድኖች እና በመደበኛ የህብረቱ አገልግሎት አማካኝነት ነው፡፡
ተማሪዎችን ደቀመዝሙር ለማድረግ እና ለመባዛት፣ ኢቫሱ ዋና ስልት አድርጎ እየተገበረ ያለው የንዑስ ቡድኖች ፅንሰ ሀሳብን ነው፡፡ ተማሪዎች በቡድናቸው ሲገኛኙ ከሚጠያየቁት የማደጊያ ግቦች አንዱና ዋናው የምስራቹን በዙሪያቸው ላሉ ሌሎች ሰዎች የማድረስ ሐላፊነታቸውን እየተወጡ እንደሆነ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ የእግዚአብሔርን ቃል ለመታዘዝ ያጠናሉ፤ አብረው ያመልካሉ፤ ይፀልያሉ እንዲሁም ህብረተሰብ ይፈጥራሉ፡፡ በዚሁ መሰረት ነው በጥቅምት ወር በወላይታ ዘጠኝ፤ በሚዛን ቴፒ አምስት፤ በወልቂጤ አራት፤ በአሶሳና ደብረታቦር በእያዳንዳቸው ሶስት፤ በሌሎች አራት ካምፓሶች ሁለት ሁለት እና በስድስት ካምፓሶች አንድ አንድ ተማሪዎች ወደ ጌታ የመጡት፡፡
እነዚህ አዳዲስ አማኞች በኢቫሱ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች፣ በተማሪዎች እና በአቅራቢያቸው በሚገኝ የወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያናት ክትትል እየተደረገላቸውና መሰረታዊ የክርስትና እምነቶችን እየተማሩ ይገኛሉ፡፡ ተምረው ሲጨርሱ በአቅራቢያቸው በሚገኝና በሚመርጡት የወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ እንዲያድጉ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርት እንዲማሩና እንዲጠመቁ ይደረጋል፡፡
የጥቅምት ወር፣ ተማሪዎች በአብዛኛው ትምህርት ለመጀመር ወደ ካምፓስ የሚሔዱበት፣ በአንዳንድ ቦታዎችም ሀገራዊ ያለመረጋጋት የነበረበት ወር መሆኑም ይታወቃል፡፡ በዚሁ ምክንያት ትምህርትም ያልተጀመረባቸው ብዙ ግቢዎች ቢኖሩም እግዚአብሔር ግን በተማሪዎች እየተጠቀመ መንግስቱን እያሰፋ ይገኛል፡፡ ለዚህም መላው የኢቫሱ ቤተሰብ እንዲሁም ጠቅላላው አማኝ እግዚአብሔርን እንድታመሰግኑ፤ በተጨማሪም የቀረውን እጅግ በጣም ብዙ መኸር ለመሰብሰብ የሚሆን ሀይል እንዲሰጠን፤ የማያምኑ ሰዎች ዓይን እንዲያበራ ፤ ለኢትዮጵያ መረጋጋትና ዘለቄታዊ መፍትሔ እንድትፀልዩ በጌታ ፍቅር እንጠይቃለን፡፡