“ መከሩስ ብዙ ነው፥…..” ሉቃስ 10፡2
የቀደሙ የዩኒቨርሲቲ ወንጌላውያን ክርስቲያን ተማሪዎች፣ ለተመደቡበት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ራሳቸውን የክርስቶስ መልእክተኛ አድርገው ይቆጥሩ እንደነበር የጽሑፍ መረጃዎች ይናገራሉ፡፡ ለህትመት እየተዘጋጀ ያለው የኢቫሱ የታሪክ ሰነድም ይኼን እውነት ከባለታሪኮቹ አንደበት ቀድቶ እንዲህ ያስነብበዋል፡-
“እኛ የካምፓስ ወንጌላውያን ነን፡፡ . . . እኛ እያለን እግዚአብሔር ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሌላ የወንጌል መልዕክተኛ አይልክም፤ ወንጌልን ለአቻዎቻችን መመስከር አለብን!”
ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላም የካምፓስ ወንጌላውያን ክርስቲያን ተማሪዎች፣ የወንጌል መልእክተኛ መሆናቸውን ቀጥለዋል፡፡ ኢቫሱ፣ እንደ ሀገር አቀፍ የተማሪዎች አገልግሎት፣ ይኼን ስራ የማስቀጠል ሃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል፡፡ ለዚህ ነው፣ መሪ ሐሳቡ፣ “በካምፓስ ውስጥ ኢየሱስን መኖር፤የኢየሱስ ምስክር መሆን” የሆነው፡፡
የወንጌል መልእክተኝነቱ ሥራ ቀጥሎ፣ በኅዳር ወር በሀገር አቀፍ ደረጃ በሰላሣ አምስት (35) ካምፓሶች ውስጥ ሁለት መቶ አስራ ዘጠኝ (219) ተማሪዎች ጌታን ተቀብለዋል፡፡ እነዚህ ወንድሞችና እህቶች በዋናነት ወደ ጌታ የመጡት በተማሪዎችና በክርስቲያን የተማሪ ህብረቶች ውስጥ በሚካሔድ የንዑስ ቡድኖችና መደበኛ የህብረቱ አገልግሎት አማካኝነት ነው፡፡
በዚህ ወር በአብዛኛው በካምፓሶች ያለመረጋጋት የነበረ ሲሆን፤ ከዚህም የተነሳ በአንዳንድ ካምፓሶች በተደጋጋሚ ተማሪዎች ከግቢ ሲወጡና ሲመለሱ መቆየታቸውን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተነገረ ከመሆኑም በላይ አብዛኞቹ የኢቫሱ የካምፓስ ሙሉ ጊዜ አገልጋዮችና የተማሪ መሪዎች ገልፀዋል፡፡ ነገር ግን በእንደዚህ አይነት ያለመረጋጋት ባለበት ሁኔታ ውስጥ የእግዚአብሔር መንፈስ የመከሩን ስራ በታዘዙ ቅዱሳን ተማሪዎች አማካኝነት ወጣቶችን ከዘላለም ጥፋት እየታደገ ይገኛል፡፡
ተማሪዎችን በደቀመዝሙር ሕይወት ለማሣደግና ለመባዛት፣ ኢቫሱ ዋና ስልት አድርጎ እየተገበረ ያለው አሠራር የንዑስ ቡድን አገልግሎት ጽንሰ ሀሳብን ነው፡፡ ተማሪዎች በቡድናቸው ሲገናኙ ከሚጠያየቁት የማደጊያ ግቦች መካከል የምስራቹን በዙሪያቸው ላሉ ሌሎች ሰዎች የማድረስ ሐላፊነታቸውን እየተወጡ እንደሆነ ማወቅ አንዱና ዋናው ነው፡፡ በተጨማሪም፣ የእግዚአብሔርን ቃል ለመታዘዝ ያጠናሉ፤ አብረው ያመልካሉ፤ ይፀልያሉ እንዲሁም የቅዱሳን ማሕበር እንደመሆናቸው የህብረት ህይወትን ይኖራሉ፡፡
እንዳለፈው ወር ሁሉ፣ በኅዳር ወርም በካምፓስ ወንጌላውያን ክርስቲያን ተማሪዎች፣ የወንጌልን የምሥራች ለሰዎች የማድረስ ስራው ቀጥሏል፡፡ የምስክርነት ስራውን ተከትሎ፣ በተለያዩ ግቢዎች ተማሪዎች ጌታን የግል አዳኛቸው አድርገው ተቀብለዋል፡፡ በሪፖርቱ ከተካተቱት ግቢዎች መካከል፣ በድሬዳዋ ሃያ ስድስት (26)፤ በሐዋሳ ሃያ ሁለት (22)፤ በአምቦ አስራ አምስት (15)፤ በደብረ ማርቆስ አስራ ሶስት (13)፤ በደብረ ታቦር አስራ ሁለት (12)፤ በጎንደርና አርባ ምንጭ በእያንዳንዳቸው አስራ አንድ (11)፤ በወልድያ፣ ስድስት ኪሎና ባህርዳር በእያዳንዳቸው ዓስር፣ በድምሩ ሰላሣ (30)፤ በሌሎች ሶስት ካምፓሶች በእያዳንዳቸው ሰባት፣ በድምሩ ሀያ አንድ (21)፤ በወልቂጤ አምስት (5)፤ በሌሎች ሁለት ካምፓሶች በእያንዳንዳቸው ሶስት፤ በድምሩ ስድስት (6)፣ በሌሎች አራት ካምፓሶች በእያንዳንዳቸው ሁለት፤ በድምሩ ስምንት (8)፣ እንዲሁም በሌሎች አራት ካምፓሶች በእያንዳንዳቸው አንድ ተማሪ፤ በድምሩ አራት (4) ተማሪዎች ይገኙበታል፡፡ ክብሩ ለሥራው ባለቤት ለእግዚአብሔር ብቻ ይሁን!!
በኅዳር ወር ወደ እግዚአብሔር መንግስት የተጨመሩት አዳዲስ አማኞችና በጥቅምት ወር ወደ ጌታ የመጡት አርባ አንድ (41) ተማሪዎች በኢቫሱ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች፣ በተማሪዎችና በአቅራቢያቸው በሚገኙ የወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያናት በኩል ክትትል እየተደረገላቸውና መሠረታዊ የክርስትና እምነት ትምህርቶችን እየተማሩ ይገኛሉ፡፡ ተምረው ሲጨርሱ በአቅራቢያቸው በሚገኝና በሚመርጡት የወንጌላውያን አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እንዲያድጉ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርት እንዲማሩና እንዲጠመቁ ይደረጋል፡፡
ከላይ በዝርዝር የተጠቀሰው ቁጥር በካምፓስ ውስጥ ጌታን የግል አዳኛቸው አድርገው የተቀበሉ ተማሪዎችን ብቻ የሚያካትት እንደሆነ አንባቢ ልብ ይሏል፡፡ በካምፓስ ተማሪዎች አማካኝነት ከግቢ ውጪ የሚካሄዱ የወንጌል ምስክርነት ስራዎች እንደሚካሄድ ይታወቃል፡፡ በጥቅምትና በኅዳር ወር በተካሄዱ የወንጌል ምስክርነት ሥራዎች፣ ቁጥራቸው የበዛ ሰዎች የወንጌልን የምሥራች ሰምተዋል፡፡ በቁጥር ብዙ የሆኑ ሰዎችም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የግል አዳኛቸው አድርገው ተቀብለዋል፡፡ ከአጥቢያ ቤተክርስቲያናት ጋር እንዲገናኙም ተደርገዋል፡፡ ከካምፓስ ውጪ የተካሄዱ የወንጌል ምስክርነት ስራዎችን አስመልክቶ ራሱን የቻለ ዝርዝር ዘገባ በቀጣይ ይዘን እንደምንቀርብ ቃል እንገባለን፡፡
በኅዳር ወር በሀገሪቱ በተለይም በካምፓሶች አካባቢ ያለው ሀገራዊ አለመረጋጋት እየተስፋፋና መልኩን እየለወጠ የመጣበት ወር መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚሁ ምክንያትም ይህ ዜና በሚፃፍበት ጊዜ እንኳን ትምህርት የተቋረጠባቸው ካምፓሶች በቁጥር ብዙ ናቸው፡፡ ስለዚህም ቅዱሳን በያላችሁበት ቦታ በጋራና በግል የፀሎት ጊዜያቶቻችሁ እግዚአብሔር መፍትሔን እንዲያመጣ፣ በጉዳዩ የመፍትሔ አካላት ለሆኑ ሁሉ ማስተዋልን እንዲሰጥ እንድትማልዱ ኢቫሱ ጥሪውን ያቀርባል፡፡ በተጨማሪም፣ ቅዱሳን ተማሪዎች በዚህ አይነት ግራ በሚያጋባ ሁኔታ ውስጥ ሲያልፉ ክርስቲያናዊ ምርጫን እንዲመርጡ፤ ውሳኔ እንዲወስኑ የእግዚአብሔር መንፈስ ጥበብና ማስተዋል እንዲሰጣቸው እንድትለምኑ እናሳስባለን፡፡ እንዲሁም አዳዲስ ወደ መንግስቱ ስለ ተጨመሩ ወጣቶች እግዚአብሔርን እንድታመሰግኑ፤ የቀረውን እጅግ በጣም ብዙ መኸር ለመሰብሰብ የሚሆን ኃይል እንዲሰጠን፤ የማያምኑ ሰዎች ዓይን እንዲያበራ፤ የዳኑትም በቃሉ እውነት እንዲተከሉ እንድትፀልዩ በጌታ ፍቅር እንጠይቃለን፡፡