የ2010 ዓ.ም የመጀመርያው የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ተማሪዎችና ምሩቃን ማሕበር (ኢቫሱ) የሙሉ ጊዜ አገልጋዮቹን አቅም የሚያጎለብትበት ስልጠና ተካሔደ፡፡ ስልጠናው በቅርቡ ለዚሁ አላማ በለገጣፎ አካባቢ በተከራየው የስልጠና ማዕከል ውስጥ ለአስራ ሁለት ቀናት ማለትም ከዕረቡ መስከረም 3 እስከ 15, 2010 ዓ.ም ተካሒዷል፡፡
ስልጠናው፣ መላው የኢቫሱን አገልጋዮች በሶስት ቡድን በመክፈል የተካሄደ ሲሆን፤ የመጀመርያው በዚህ 2010 ዓ.ም የተቀላቀሉ አገልጋዮች፣ ሁለተኛው ነባር እና በቅርብ አመታት የተቀላቀሉ አገልጋዮችን እና በመጨረሻም ሶስተኛው የክልል አስተባባሪዎችን፣ የክፍል አስተባባሪዎችን እና የዲፓርትመንት መሪዎችን ያካተተ ነበር፡፡
በዚሁም መሰረት በአብዛኛው በየቡድኑ እንደዚሁም በአንድነት አስፈላጊ የሆኑ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች ተሰጥተዋል፡፡ ከተሰጡ ትምህርቶች መካከል ለመጀመርያው ቡድን መሰረታዊ የሆኑ ማለትም ከመፅሐፍ ቅዱስ ጋር የሚኖር ቁርኝት፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት ስለመጠበቅ፣ ሰቨን ፒላርስ (የክርስትና መሰረታውያን)፣ የንዑስ ቡድን አሰተባባሪዎችን ስለመምራት፣ የኢንዳክቲቭ የመፅሐፍ ቅዱስ አጠናን ዘዴ እናም ፆታዊ ንፅህና በመሳሰሉ ርዕሶች ላይ ስልጠና የወሰዱ ሲሆን፤ በመጨረሻም የማርቆስ ወንጌልን የመጀመርያ ክፍል በማኑስክሪፕት የአጠናን ዘዴ ሰፊ ጊዜ ወስደው አጥንተዋል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ ለሁለተኛው ቡድን ከመፅሐፍ ቅዱስ ጋር የሚኖር ቁርኝት፣ መፅሐፍ ቅዱሳዊ አመራር፣ ክርስቶስን ያማከለ ስብከት፣ አምላካዊ ቃል ኪዳን በሚሉ ርዕሶች ላይ ሰፋ ባለ ሁኔታ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም በስፋት የ2009 ዓ.ም የስራ ክንውን
የተገመገመበት ለሚቀጥለው 2010 ዓ.ም አቅጣጫ የተያዘበት ገንቢ ስብሰባ ተካሂዷል፡፡
ሶስተኛውም ቡድን በተመሳሳይነት ከሁለተኛው ቡድን ጋር ለአምስት ቀናት ክርስቶስን ያማከለ ስብከት እና አምላካዊ ቃል ኪዳን በሚሉት ርዕሶች ላይ የተሰጠውን የስልጠና መርሀ ግብር የተሳተፈ ሲሆን፤ ነገር ግን በዋናነት የ2009 ዓ.ም የየክልሎችን እና የዋናው ቢሮን የዕቅድ አፈፃፀም በሰፊው ገምግሟል እንዲሁም የ2010 ዓ.ም ዕቅድ ላይ በዝርዝር ተነጋግሯል፡፡
በተጨማሪም በተከታታይ ምሽቶች በነባር እና አዲስ በሚገቡ አገልጋዮች መሀከል የልምድ ልውውጥ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም በቀድሞ አመታት የኢቫሱ አገልጋይ የነበሩ አሁን በተለያየ አገልግሎት ውስጥ የሚገኙ የተወደዱ ወንድሞች እና እህቶች ልምዳቸውን አካፍለዋል እንዲሁም ስልጠናዎችን ሰጥተዋል፡፡ ከነዚህም መካከል በ50ዎቹ ከኢቫሱ መስራቾች መሀከል አንዱ የነበሩት ጋሽ ሰለሞን ከበደ፤ በስደቱ ጊዜ የኢቫሱ አገልጋይ የነበሩት መጋቢ ጥሩወርቅ መስፍን እና ጋሽ አይናለም ታደሰ፤ በዘጠናዎቹ አጋማሽ የኢቫሱ ዋና ፀሀፊ የነበረው ወንድም መሳይ እምሩ እናም የመሀከላዊ ቢሮ አስተባባሪ የነበረችው እህታችን ቅድስት ባህሩ ነበሩ፡፡
በመጨረሻም በ2010 ዓ.ም አመታዊ የኢቫሱ ተማሪ መሪዎች ጉባኤ የተካሔደበት መሪ ሐሳብ ’ኢየሱስ ክርስቶስን በካምፓስ መኖርና መመስከር’ የሚለው ሀሳብ ላይ አፅንኦት ተሰጥቶ የትኩረት አቅጣጫዎች እና የየዕለት የዕቅድ ትግበራዎች በዚህ ሀሳብ ማጠንጠኛነት የተቃኙ እና ትኩረት ያደረጉ እንዲሆኑ አቋዋም ተይዟል፡፡ በመጨረሻም ለሁለት ቀን የፆም ፀሎት ተደርጎ መርሀ ግብሩ በእግዚአብሔር አሳኪነት በታላቅ እጅ መያያዝ እና በጋለ መንፈስ ተጠናቋል፡፡