Oct262017Newsበየካቲት 2009 ዓ.ም የተጀመረው የኢቫሱን የቀጣይ አምስት አመታት ስልታዊ ዕቅድ የመንደፍ ስራ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ተሸጋግሯል፡፡ ባሣለፍነው ቅዳሜ ጥቅምት 11/2010 ዓ.ም በሠንዳፋ የልጆች ዕድገት ስልጠና እና ምርምር ማዕከል ከተማሪዎች፣ ከምሩቃን፣ ከኢቫሱ ቦርድ አባላት እና ከሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የተወከሉ 18 ሰዎች በተገኙበት የእቅዱ ስልት እና ግብ የማስቀመጥ ስራ ተከናውኗል፡፡ በዚሁ ጉባኤ ላይ፣ ሁለት የስልታዊ እቅድ ቅየሳው ትሩፋት የሆኑ ዶክመንቶች ቀርበው ገንቢ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ የመጀመርያው የኢቫሱ ጠቅላላ ማንነት፣ ምንነት እና ዐላማ በዝርዝር የተተነተነበት ባለ 3 ገፅ ዶክመንት ሲሆን፤ ዶክመንቱን ለማዘጋጀት ከአርባ አንድ በላይ፣ ከተማሪዎች፣ ምሩቃን እና የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የተውጣጡ ሰዎች ተሣትፈውበታል፡፡ የስልታዊ እቅድ ዝግጅቱ ሁለተኛ ውጤት የሆነው ዶክመንት፣ ከአምስት ባለድርሻ አካላት የተወጣጡ አንድ ሞቶ ሃምሳ ስምንት(158) ሰዎች ተካፋይ ሆነውበታል፡፡ ዶክመንቱ፣ ባለ ስድስት(6) ገጽ ሰነድ ሲሆን፣ የኢቫሱን ጥንካሬ፣ ድክመት፣መልካም አጋጣሚና እንቅፋቶች ያካተት ነው፡፡ በእነዚህ ሁለት ዶክመንቶች መነሻነት፣ የአምስት አመቱ ግብ ምን መሆን እንደሚኖርበት እንዲሁም ግቡን ለማሣካት መከተል የሚኖርበትን ስልት በቡድን በመከፋፈል ተሰርቷል፡፡ በእለቱ፣ የቀጣይ ስልታዊ እቅዱ ንድፍ አርቃቂ ኮሚቴ አባል እና የኢቫሱ የቦርድ አባል የሆኑት አቶ ፀጋዬ ምትኩ ኮሚቴው ያከናወናቸውን ተግባራትና ቀሪ ስራዎችን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ አቶ ፀጋዬ፣ እቅዱ ይጠናቀቃል ከተባለበት ከነሐሴ 2009 ዓ.ም ያለፈው፣ የኢቫሱን የማንነትና የአላማ ዶክመንት ማዘጋጀት ከታሰበውና ከታቀደው ጊዜ በላይ በመውሰዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ሲናገሩ፣ የቀጣይ አምስት አመት ስልታዊ እቅድ ዝግጅቱ በመፋጠን፤ ዶክመንቱም በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን አስታውሰው “ይህን ዕቅድ ሠርተን መደርደርያ ላይ ካስቀመጥነው እንደኛ የከሰረ ሰው የለም” በማለት ዋናው ነገር እቅዱን ትርጉም ባለው ሁኔታ ወደ መሬት ማውረድ መቻሉ ላይ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ በተመሣሣይ፣ የስልታዊ እቅዱ ንድፍ አርቃቂ ኮሚቴ አባል የሆኑት ወንድም ተወልደ ሁልጊዜ፣ በግልም፣ እንደ ቤተክርስቲያንም አንዲሁም እንደ ኢቫሱ የተሞረድን ስለታም መሆን እንደሚገባን የሚያሣስብ አጭር መልእክት፣ መጽሐፈ መክብብ 10፡10 መነሻ በማድረግ አካፍለዋል፡፡ ክፍሉን መሰረት በማድረግም፣ ለምንሰራው ስራ ትኩረት መስጠት፤ የጊዜውን ነገር መለየትና፤ ወደ ስራው ባለቤት በፀሎት የመቅረብን አስፈላጊነት አመላክተዋል፡፡ በመልእክቱ ማጠቃለያም፣ ይህ ጊዜ ለኢቫሱ የመሣል’ ጊዜው መሆኑንም በማሳሰብ ተናግረዋል፡፡ የቀጣይ አምስት አመት ስልታዊ እቅድ ንድፍ ተረቆ ሲያልቅ፣ ለኢቫሱ እንደ ተቋም መጠነ ሰፊ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ ከሚሰጣቸው ፋይዳዎች መካከል ጥርት ያለ የአገልግሎት አቅጣጫዎች ያሳያል፣ ያለውን የሰው፣ የገንዘብ እና የንብረት ሀብት ውጤት እና ግብ ተኮር በሆነ መልኩ ለመጠቀም ይረዳዋል፣ አገልግሎቱ ዘመኑን የዋጀ እንዲሆን ያግዛል፡፡ በተጨማሪም፣ እስካሁን በአገልግሎቱ ያልተካተቱ ነገሮችን በማሣየት እንዲካተቱ ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ በአጠቃላይ፣ ስልታዊ እቅዱ በሥራ ላይ ሲውል፣ ኢቫሱ፣ የአገልግሎት ቅርጹን እንዲያስተካክል፣ ብሎም ውጤታማነቱ እንዲጨምር ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡ Category: NewsBy EvaSUEOctober 26, 2017Share with FacebookShare with TwitterShare with WhatsAppShare with PinterestShare with LinkedIn Author: EvaSUE Post navigationPreviousPrevious post:የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ኢቫሱን ተቀላቀሉNextNext post:Zelalem Abebe has been appointed as IFES-EPSA Regional SecretaryRelated PostsEvaSUE-Associates WebinarJanuary 22, 2021BUSINESS FOR KINGDOM IMPACT COMPETITION 2020October 23, 2020Life Interruption የሕይወት መቋረጥ/መቆራረጥMay 7, 2020ከቃሉ ጋር መገናኘትApril 30, 2020God exists, and He is good.April 23, 202030 የምህረትና የቸርነት ዓመታት፣May 16, 2018