በዓለማች በተከሰተው የቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ስራችን፤ ትምርታችን ፤ ዕቅድና ፕላናችን ፤ ለማናቀው ጊዜ ተቋርጧል። ታድያ ህይወት ሲቋረጥ እና ዕቅዶቻችን ሲቋረጡ እንዴት እንኑር? እንዴት ላለንበት ሁኔታ የሚመጥን የሕይወት ዘይቤ ይኑረን? የሚልጥያቄ ማንሳት፤ መልስም መሻት ጠቢብ ያደርጋል፡፡
ለዚህ ክስተት የሥነ መለኮት፣ የፍልስፍና፣የሕክምና፣የሳይንስ እና የሃይማኖት ሰዎች በተለያየ ግንዛቤ የተለያየ ትንታኔ ያስተላልፋሉ። በክርስቲያኑም ማህበረሰብ ውስጥ የእግዚአብሔር ቁጣ መገለጫ ነው ከሚለው ፤ የለም የእግዚአብሔር ሰውን መሳቢያ/ማንቂያ ደወል ነው የሚል፤ የመጨረሻ ዘመን ዛሬ ማታ ነው አለቀልን /ዓለም አለቀላት የሚል፤ የለም የተለመደ ክስተት ነው አትደናገጡ የሚሉ፥ የተለያዩ ሀሳቦች ይንሸራሸራሉ። ይህ ሁሉ መልካም ነው!
ለእኔ ግን ሕይወት ሲቋረጥ/ሲቆራረጥ እንዴት እንኑር የሚለውን ጥያቄ መመለስ የተግባር ሰው ያደርገናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም ይህንን ጥያቄ መመልስ ዛሬና ነገ የምናደርገው የምንሆነው፤ በተግባር የምናሳየው ነገር የዘላለም የሆነውን የእግዚአብሔርን መንግስት ለማስፋት የሚያዋጣው ድርሻው ብዙ ስለሆነ ነው፡፡ ለገጥመን ክስተት እውነታ እንዴት እንዘጋጅ? እንዴት እንኑር? ጊዜውን እንዴት እንጠቀምብት ? እንዴት ተግባራዊ ሰዎች እንሁን? እንዴት ክርስቶስን እናሳይ? የሚሉትን ደቀ መዝሙራዊ ጥያቄዎችን መጠየቅ ይሻላል፤ ይቀድማልም እላለሁ፡፡ ይህንን ካስቀደምን ሕይወት በሚቋረጥበት ጊዜ መለኮታዊ ምላሽ/ጣልቃ ገብነት መኖሩ (In a time of Interruption there is Divine Intervention) በጥልቀት ይገባናል። ሕይወት ሲቋረጥ ጌታ ዕቅዱ ሳይቋረጥ በሥራ ላይ ነውና።
የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወት ታሪክ ከወንጌላት ስናነብ በመቋረጥ (Interruption) የተሞሉ የታሪክ ሁነቶች በብዛት እናገኛለን። ከልደቱ ስንጀምር ሉቃስ 2፡1-5 ከአውግጦስ ቄሳር የመጣው ትዕዛዝ በቄሬኔዎስ አገዛዝተግባራዊ እንዲሆን የተወሰነው የህዝብ ቆጠራ በሰዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ያስከተለውን ማቋረጥ (Interruption) ማየት ይቻላል። ሰው ሁሉ በየቤቱ ሳይሆን በየትውልድሀገሩ እንዲቆጠር መታዘዙ በሰዎች ኑሮና ኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለውን ቀውስ ብዙ ነው፡፡በጥቂቱም ቢሆን በእኛ ሃገር ከቀያችን ውጣ፤ ወደ ትውልድ ሀገርህ ወይም ወደ ዘርህ ትውል ሂድ የሚለውን የማፈናቀል ክስተትና ቀውስ ይመስላል። በዚህ ቀውስ ውስጥ ግን እግዚአብሔር የትንቢቱን ፍፃሜ በታሪኮች ላይ ያለውን የበላይነት፣ የክርስቶስንም መወለጃ ቤቴልሔም እንዲሆን ሲያደርገው እናያለን፤ ሁኔታው የፈጠረው ቀውስ ጌታ መንግስቱን ስራ መከናወኛ የትንቢቱም መፈፀሚያ ያደርገዋል፡፡
የግብፅ ሽሽትማ ቴ 2፡13-23የማርያምና የዮሴፍ ህጻኑን ኢየሱስን ይዞ ስደት እና ለህይወት መስጋት ትልቅ መቋረጥ (Interruption) ነበር። ያውም በግዴታ፣ የማያውቁት ሃገር እና ሁኔታ ከዘመድ መራራቅ ሁለት ሜትር ሳይሆን በሺህ ኪሎ ሜትር፤ ግን በዚህ መቆራረጥ በየጊዜው የተነገሩት የትንቢት ቃላት በመፈፀም እግዚአብሔር የበላይ የታሪክ አስኪያጅ፣ አስፈፃሚ ተቆጣጣሪ መሆኑን ያሳያል፡፡ በወንጌል የተከሰቱትን ብዙ የጌታን ሕይወትና የአገልግሎት መቋረጥ (Interruption) ስናይ ውጤቱ ደግሞ እግዚአብሔር እንደ ጥበበኛ አናጢ ወይም ጠራቢ ውበት ያለው ነገር የሚያወጣበት መሆኑን ያሳያል።
በመካካል ያሉትን ትቼ የጌታ የመጨረሻ የሕይወት ጉዞ ስናይ መቋረጥ (Interruption) የሚመስል ክስተት እናያለን። የአገልግሎቱ ከፍታ ላይ ሰዎችን የማስተማር፣ የማዳን፣ የእግዚአብሔርንም መንግስት የመስበክ ብዙ ተከታዮችን በማፍራት ላይ እንዳለ፤ እንዲያውም ከሳምንት በፊት ከተማን የሚያናውጥ የድጋፍ ሰልፍ (የሆሳዕና ዝማሬ) ተከስቶ በሳምንቱ ግን ተይዞ ለፍርድ ቀርቦ ለሞት አልፎ ተሰጥቶ ሲሰቀል እንናነባለን፡፡ ይህን የሕይወት መቋረጥ ሉቃስ 24፡13-35 ላይ የተጠቀሱት ደቀ መዛሙርት የኤማሁስ መንገደኞች የሚንላችው በታላቅ ተስፋ መቁርጥ ውስጥ ሆነው ይተርኩታል። ኢየሱስ ክርስቶስ እየሰራ የነበረውን፥ እያከናወነው የነበረው ሁሉ፤ የኢየሱስ ማንነትና የአገልግሎት መገለጫ የሆኑት ሁሉ እንደተቋረጡ ነበር የሚመሰክሩት። ምስክርነታቸውም የተረዱትም ሁሉ እውነትነበር። ይሁን እንጂ የመቋረጥ (Interruption) የሚመስለውን ነገር ግን ጌታ የትንሳኤው መንገድ አድርጎታል። በመስቀሉም የተሰራው ስራ የአላማው ሁሉ ማስፈፀሚያ አድርጎታል። ኢየሱስም አብሮአቸው እንደተጓዥ መንገደኛ ተገልጦ የሚያስረዳችው ይህንኑ ነው። በአጠቃላይ በመጽሐፍ ቅዱሳችን በአገልጋዮችም ሆነ በግለሰቦች የተከሰቱትን መቋረጦች እግዚአብሔር ለክብሩ ሲያውላቸው እናያለን።
እንደ እግዚአብሔር መንግስት ዜጋ አሁን የተከሰተውንም የቫይርስ ስጋት ሆነ ወደፊት በግልም፣ በማህበርም፣ በሃገርም፣ በዓለም አቀፍም መድረክ የሚከሰቱ የሚችሉ መቋረጦች (Interruptions) ስናስብ፤ እግዚአብሔር የበላይ ሁኖ ለክብሩ፣ ለአላማው፣ ለመንግስቱ፣ ማስፊያ የሚጠቀምበት እንደሆነ መረዳት ከፍርሀት፣ ከግምት፣ እና ከመላምት ነፃ ያደርጋል። በእርሱ ታምንን ለመኖርም ያግዛል።እግዚአብሔር ይህንን ምስቅልቅል (Crisis) ዕቅዱን እና ሀሳቡን ለመፈፀም ሲጠቀምበት እኛ እንደ እርሱ ተከታዮች ይህንን እንደዕድል (Opportunity) መጠቀም ጥበብ ነው። በዚህ በተከሰተው አስችጋሪ ሁኔታ ነገሮች ቢቋረጡ፣ ቢቆራረጡ እግዚአብሔር ቀጣይ ነው እኛም ከእርሱ ጋር ቀጣይ ተቀጣጣይ መሆን ይኖርብናል። እግዚአብሔር የበላይ፤ የዚህም ሁኔታ ተቆጣጣሪ መሆኑን ከተረዳን፤ በዚህ አዲስ ሁኔታ፤ አዲስ ግንዛቤ፣ አዲስ መረዳት፣ አዲስ አመለካከት፣ አዲስ ዝማሬ ይዘን ብቅ ማለት ይገባናል። በሚለዋወጠው ዓለም በሚለዋወጠው ሁኔታ የማይለወጠውን የክርስቶስ ወንጌል ማካፈል አለብን 2 ቆሮ 4፡8-9 ።
Author: Sisay Desalegn (PhD), former staff and currently Associate at EvaSUE